ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅሩን ወደ ክልሎች ለማውረድ የሚያስችለውን ጥናት አጠናቀቀ

63

ግንቦት 15/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅሩን ወደ ክልሎች ለማውረድ የሚያስችለውን ጥናት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ተአማኒ ለማድረግ የቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ መጽደቁ ይታወሳል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ለኢዜአ  እንደተናገሩት በአዋጁ መሰረት የቦርዱን የውስጥ መዋቅርና አደረጃጀት በክልሎችም ለመተግበር የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል።

በህጉ መሰረት መዋቅር በመቀየር ና አስተዳደራዊ ስራዎችን  በመስራት  በዋናው  መስሪያ ቤትና በክልል የሰው ሃይል ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በጥናቱ መሰረት ቀደም ሲል ከፌዴራል እስከ ወረዳ በሚገኙ የምርጫ  ጣቢያዎች  የነበረውን የአደረጃጀት ችግር ለማስተካከል እንደሚሰራም አማካሪዋ ገልጸዋል።

ጥናቱ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ከላይ እስከታች በህዝብ ዘንድ  ተአማኒ  በሆነ  መልኩ  ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል የአሰራር ስርአት የሚፈጥር መሆኑም ታምኖበታል ብለዋል።

"ኢትዮጵያዊያን ተቋሙ ካደረጋቸው ዝግጅቶች አንጻር ምርጫ ቢያካሂድ እናምነዋለን”  የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ምርጫው በተአማኒነት እንዲካሄድ ቦርዱ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀረው ጊዜ ለምርጫ አስፈላጊ የሆኑ የህግና የአደረጃጀት ስራዎችን  ተግባራዊ  ለማድረግ  እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

 ምርጫ ቦርድ በህግ በተሰጠው ስልጣንና የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረግ እንጂ ምርጫ የማራዘምና መካሄድ አለበት የማለት  ስልጣን  እንደሌለውም አስረድተዋል።

ሆኖም ምርጫ ለማካሄድ በሚደረገው ዝግጅት በአገሪቷ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተጽእኖ  እንደሚያሳድር ተናግረው፤ ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ ምርጫ አስፈጻሚዎችን  በአገር ውስጥ ማሰማራትና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን  ማሰራጨትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

እነዚህን ስራዎች ለማከናወን ያለው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ከሆነ ከቦርዱ አቅም በላይ መሆኑን ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቁ ገልጸው እስከዚያ ድረስ ግን  ዝግጅቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በምርጫ ወቅት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሃሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን ማሰራጨት የተለመደ በመሆኑ፤ በቀጣዩ ምርጫ  ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ  ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅና የምርጫ ህግ ማሻሻል እንዲሁም  ከሲቪክ  ማህበራትና  ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው  ግንኙነት  ባለፉት  ወራት  የተጀመሩ ስራዎች ናቸው።

ተቋሙን በማደራጀት ተአማኒ  ምርጫ ለማካሄድ በትኩረት እየተሰራ  መሆኑንም  ወይዘሪት ሶሊያና አብራርተዋል።

ረቂቅ የምርጫ ህጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት የተደረገበት ሲሆን ሌሎች  ከሚመለከታቸው አካላት  ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ  ይጸድቃል  ተብሎ  ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም