” አመድ አፋሽ ! ”

336

ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/

ሰነፍ ነው ብለን የገመትነውን ሰው ”አህያ” ብለን የምንሳደብ ስንቶቻችን ነን? ግን አህያ ሰነፍ ነው እንዴ? መልሱ በፍፁም አይደለም የሚል ይሆናል። እንዲያውም አህያ የታታሪነት መልክም ማሳያ ነው። እንደውም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ”አህያ የሌለው ገበሬ ራሱ አህያ ነው!” ይባላል ። ለምን ?

መልሱ ግልፅ ነው ። አህያ የሌላቸው አርሶ አደሮች ሁሉንም ሸክም ሴት በጀርባዋ ወንድ ደግሞ በትከሻው ተሸክመው እለታዊ ስራዎቻቸውን ስለሚያከናውኑ ነው። አህያ ያላቸው ግን የስራ ጫናውን በአህያው ላይ ጥለው እፎይ ይላሉ።

የአህያ አገልግሎት በገጠር አካባቢዎች ላይ ብቻ የተወሰነ መስሎ የሚሰማን ከሆነም ተሳስተናል። በአዲስ አበባ መርካቶ የገበያ ስፍራ ብቻ በቀን በአማካይ 3ሺህ አህዮች እህልና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ተሸክመው ገብተው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ተሸክመው እንደሚወጡ ያጫወቱኝ የጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ፈንታ ናቸው ።

ስለዚህ የአህያ አገልግሎት ከገጠር እስከ ከተማ በሌላ አነጋገር  ”ከባሌ እስከ ቦሌ” የዘለቀ ነው ብሎ መውሰድ ተገቢነት አለው ።

እያንዳንዱ አህያ በቀን በአማካይ 200 ብር ለባለቤቱ ገቢ ያስገኛል። 3 ሺህ አህዮች በዓመት የሚያስገቡት ገቢ ሲሰላ ደግሞ 219 ሚሊዮን ብር  ይደርሳል። ስለዚህ አህያ የላቀ ትርጉም ያለው የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው ።

ኢትዮጵያ በአህያ ብዛት ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ የአህዮች ቁጥር ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወደ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን በማደጉ ከዓለም የአንደኝኛነቱን  ደረጃ 6 ሚሊዮን አህዮች ካሏት ከቻይና ተረክባለች።

የአህያ ዝርያዎቻችን አምስት ናቸው። በመካከለኛውና በሰሜን የሀገራችን ክፍል በብዛት የሚገኘው የአህያ ዝርያ አቢሲኒያ ዶንኪ በመባል ይታወቃል። ሌሎቹ የአህያ ዝርያዎች በአንፃራዊ መልኩ ግዙፎችና የጅማ፣ የኦጋዴን፣  የሲናርና የአሶሳ ዶንኪዎች ተብለው እንደሚጠሩ የፕሮጀክቱ ሃላፊ ይናገራሉ ።

8 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአህያ ሀብታችን እንደ መርካቶዎቹ አህዮች በቀን 200 ብር የሚገመት ገቢ ካስገኙ፣ ወጪ ከቀነሱና ተመጣጣኝ ግምት ያለው አስተዋፅኦ ካበረከቱ በዓመት በአማካይ በኢኮኖሚው ላይ  በቢሊዮን ብር የሚገመት  ድርሻ ያበረክታሉ ።

ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይሄንን ለማሳካት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የችግሩ ምንጭ እኛው ተጠቃሚዎች ራሳችን ነን። በአመለካከትም ሆነ በተግባር ለአህያ ያለን አስተሳሰብ የተዛነፈ ነው። ተገቢውን እንክብካቤ አናደርግላቸውም። እንዲያውም ባገለገሉን ሽልማታቸው ዱላ አድርገን እናስባለን ።

አህያውን ያልመታ ሰው ቢያጋጥም እንኳን ባለመማታቱ ”አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ብለን እንተርትበታለን። ፈሪ እንዳይባል ያለርህራሄ አህያውን እንዲነርተው የሚያነሳሳ አባባል ነው ። ባገለገለ አመድ አፋሽ እናደርገዋለን-አህያ።

የተሻለ መኖ ቢኖረን እንኳን ለቀንድ ከብቶች እንጂ ለጋማ ከብቶች እጃችን አይፈታም።  ደህና ጉረኖ ሰርተን ስለማናጉራቸው ደግሞ ብዙ ጊዜ በጅብ ይበላሉ። የምንጭናቸውም አቅማቸውን ታሳቢ አድርገን አይደለም ።

በተለይ በስምጥ ሸለቆ አካካቢ ዕቃ ጭነው ጋሪ በሚጎትቱ አህዮች ላይ ከ15 በላይ ሰዎች መጫን የተለመደ መሆኑን አቶ አለማየሁ ፈንታ ይናገራሉ። ከጭነት ብዛት ደግሞ አብዛኛዎቹ ጀርባቸውና እግራቸው የቆሳሰሉ ገጣባዎች ናቸው ።

ይህ ሁሉ ተዳምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ አህዮች በህይወት የመኖር ዕድሜአቸው ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ ነው። እንደ  አቶ አለማየሁ ገለፃ በአደጉ አገራት  የአህያ አማካይ እድሜ 37 ዓመት ነው።

መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚገኙ አህዮች አማካይ ዕድሜ 25 ዓመት ሲሆን የኛው አገር ሚስኪን አህዮች አማካይ ዕድሜ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ9 ዓመት የዘለለ አልነበረም። ዕድሜ ለጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት በቅርቡ የአህዮቻችን ዕድሜ ወደ 15 ከፍ እንዲል አድርጎታል። ያም ሆኖ ግን አሁንም ከሌሎች አገራት አህዮች አንፃር ስንመለከተው የኛዎቹ አህዮች ዕድሜ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ለአህዮቻችን ዕድሜ ማጠር አያያዛችን፣ አጠቃቀማችንና የአስተሳሰባችን ውሱንነት ቀዳሚው ተጠቃሽ ምክንያት ሲሆን ኮሶና ወስፋት የመሳሰሉት የውስጥና መዥገርና ቅማል የመሳሰሉ የውጭ ጥገኛ ተህዋሲያን የሚያስከትሉት ጉዳትም ቀላል አይደለም።

በአህዮች ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል የተመለከቱት ፕሮፌሰር ፍስሃ ገብረአብ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ምሁር “The donkey sanctuary” ከተባለ የእንግሊዝ ድርጅት ጋር በመነጋገር ሐምሌ 1986 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ለአህዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ የጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት እንዲቋቋም አደረጉ።

ፕሮጀክቱ ዓመታዊ በጀቱ 60 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የነበረ ሲሆን የቢሾፍቱ አካባቢን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ 10 ወረዳዎች፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶቸን በመክፈት የተሟላ የህክምና አገልግሎት በመስጠት 25 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በእነዚህ አካባቢዎች በዓመት ሁለት ጊዜ ለ170 ሺህ አህዮች  የህክምና አገልግሎት በመስጠት የተሟላ ጤንነት እንዲኖራቸው አድርጓል ።

ህብረተሰቡ በአህያ አያያዝ ላይ የነበረው የግንዛቤ ውሱንነት በአንፃራዊ መልኩ እንዲሻሻል በማስተማር ጭምር የአህዮቻችን አማካይ ዕድሜ ከ9 ዓመት ወደ 15 ዓመት ማሳደግ እንደተቻለ ከአቶ አለማዮህ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

በአህያ ላይ ያለውን የተዛባ  አመለካከት ለማስተካከል ከአጫጭር ስልጠናዎች ባሻገር እያዝናኑ የሚያስተምሩ ከ7 ሺህ በላይ መፅሐፍትን አሳትሞ በማሰራጨትና በየገበያው ቦታዎች ህዝብን ሰብስቦ በማስተማር ፕሮጀክቱ ሰፊ ጥረት አድርጎ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማግኘቱን ሃላፊው ያስረዳሉ።

ጥረቱ የአህዮችን በቁስል የመጎዳት ምጣኔ  ከ24 በመቶ  ወደ 5 በመቶ ዝቅ አድርጎታል።

የተሟላ የህክምና ላባራቶሪ፣ የቀዶ ጥገና ክፍልና የአህዮች ማቆያ ክፍል ያለው የህክምና ማእከል በቢሾፍቱ ከተማ ይገኛል።  በየቀኑ ወደ መርካቶ ገብተው የሚወጡ 3 ሺህ አህዮች ለመንከባከብ ሲባል ደግሞ እዚያው መርካቶ ላይ ተመሳሳይ የአህዮች ህክምና መስጫ ማእከል ተከፍቷል።

በቢሾፍቱው የህክምና ማእከል በዓመት በአማካይ 8 አህዮች በቀዶ ጥገና ህክምና እንዲወልዱ ይደረጋል። ምክንያቱ ደግሞ አህያዋ አካሏ ሳይጠነክርና ማህፀኗ ሳይሰፋ ቶሎ እንድትወልድላቸው  በማሰብ ብቻ ባለቤቶቿ በለጋ እድሜዋ  እንድትጠቃ  ስለሚያደርጓት ነው።

ከአቅሟ በላይ የሆነው እርግዝናዋ ለሞት እንዳያጋልጣት በወፍራም ፍራሽ ላይ ተኝታ እንድትወልድና  ተገቢው እንክብካቤ አግኝታ እንድታገግም ይደረጋል። የመተንፈሻ አካል ችግር ያጋጠማቸው አህዮችም ግሉኮስ ተተክሎላቸው እንዲድኑ ይደረጋል።

በጅብ ተነክሰው ሙዳ ስጋ የተነሳባቸው አህዮች በማእከሉ ታክመው መውጣት ደግሞ የተለመደ ነው። በመኪና አደጋም ሆነ ጋሪ ሲጎትቱ ለጉዳት የተዳረጉ አህዮች ከመጠን በላይ ደም ፈሶባቸው ለሞት እንዳይጋለጡ ደግሞ በፍጥነት ከአደጋው ቦታ ደርሶ ወደ ህክምና ማእከሉ የሚያመላልስ የአህያ አምቡላንስ መኖሩን አቶ አለማየሁ ይናገራሉ ።

ስለ እንክብካቤው ጉዳይ ሲነሳ በዚች ደሃ አገር ይህ ሁሉ ለአህያ ይደረጋል ሲባል የቅንጦት ይመስላል። ግን አይደለም። አህያ ለሰው ልጆች ከምትሰጠው ጥቅምና አገልግሎት አንፃር ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም።

አርሶ አደራችን ውሃ ቀድቶ በበርሜልና በጀሪካን የሚያመላልሰበት፣ ዘርን ወደ ማሳና ምርትን ደግሞ  ከአውድማ ወደ ቤት የሚያጓጉዝበት፣ አሸዋና ማገዶ የሚጭንበትና ከሰው አቅም በላይ የሆኑ የሸክም ስራዎች ለሚያከናውነው አህያ ከዚህም በላይ እንክብካቤ ይገባዋል የሚል ሃሳብ እንዳላቸው ሃላፊው ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖለስ መምሪያ የትራፊክ ደህንነት ዲቪዥን ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እስማኤል አባድር እንደሚሉት ከሆነ ግን  በዞኑ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በአህያ ጋሪ ላይ ዕቃና ከ11 ሰዎች በላይ በመጫን በእንሰሳት ሃብቱ ላይ ያልተገባ ጉዳት የሚደርስበት አጋጣሚ በርካታ ነው።

አልፎ አልፎም ጋሪ ከጋሪና ጋሪ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋጨ በሰውና በአንሰሳት ህይወት ላይ የሞት አደጋ እንደሚያጋጥም የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተሩ፤ አህዮችን  በአግባቡ በመጠቀም እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል ባይ ናቸው።

ወደ ጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት ሳመራ የአሁኑ ሁለተኛ ጊዜዬ ነው። መጀመሪያ ቢሾፍቱ ላይ ተገኝቼ  የአህያ ህክምና ማእከሉን የጎበኘሁት ከ10 ዓመት በፊት ነበር ። ያኔ ተቀብለው ያስተናገዱኝ ታለቁ ሰው የማእከሉ መስራች ፕሮፌሰር ፍስሃ ገብረአብ በህይወት የሉም። ነብስ ይማር ! ስራቸው ግን ህያው ነው ። 

በአህያ  ሀብታችን ላይ የታየው መሻሻል ጥሩ ስሜት ሲያሳድርብኝ ፕሮጀክቱ ስራውን ለማቋረጥ የቀረው አንድ ዓመት ተኩል ብቻ መሆኑን ሲነገረኝ ደግሞ ሰውነቴ ድንጋጤ ወረረው ። የሚመለከተው አካል ፈንድ አፈላልጎ እንዲያስቀጥለው ምኞቴ ነው ።

በህይወት የሌሉት ታላቁ ሰው ፕሮፌሰር ፍስሃ ገብረአብ ከ10 ዓመት በፊት የተናገሩትን በማስታወስ ፅሁፌን ልቋጭ።

”ሰነፍ ሰው ለምን አህያ ተብሎ እንደሚሰደብ ይገርመኛል። አህያ በጦርነት ወቅት ስንቅና ትጥቅ በማጓጓዝ ለሀገር ሉአላዊነት ድርሻዋን የምታበረክት፣ በድርቅ ወቅት የእርዳታ እህልን በማመላለስ ውድ የሰው ህይወትን የምትታደግና በሰላም ጊዜ ውሃና ማገዶ ተሸክማ በማቅረብ ኑሮአችን እንዲቃና እገዛ የምታደርግ የታታሪዎች አርአያ እንጂ የስንፍና መገለጫ አይደለችም። ”

  .

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም