የመምህራን የኢኮኖሚ ጥያቄዎች የተማሪዎችን ፈተና ከማስተጓጎል ጋር እንደማይገናኝ ተገለጸ

128

አዲስ አበባ ግንቦት 15 / 2011  አገር አቀፍና  ክልላዊ  ፈተናዎች  መምህራን  በሚያነሷቸው  የኢኮኖሚ  ጥያቄዎች  ምክንያት እንደማይስተጓጎሉ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የመምህራን ማህበር በበኩሉ የመምህራን የቤት ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝ ቃል መገባቱን ገልጿል።

የ2011 ዓ-ም አገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎች ከሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠት ይጀምራሉ።

በዚህ መሰረት ከሰኔ 3 እስከ 5 የ10ኛ ከሰኔ 6 እስከ 11 የ12ኛ ክፍል እንዲሁም ከሰኔ 12-- 14 የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በአገር አቀፍ ደረጃ ለመስጠት መርሃ ግብር ወጥቷል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ገብረየሱስመምህራኑ የሚያነሷቸው የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም ተማሪዎች አገር አቀፍ ፈተናዎችን እንዳይፈተኑ መቀስቀስ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ሀሳቡ የብዙ መምህራን አለመሆኑንም በመግለጽ።

የሙያውን ስነምግባር አክብረውና ሙያቸውን ወደው የሚሰሩ ምስጉን መምህራን ካላቸው አነስተኛ ገቢ ላይ ቀንሰው ለተማሪዎች ምገባ የሚያውሉ መሆኑንም ነው ያነሱት።

መምህራን የኢኮኖሚ ጥያቄያቸውን ለማስመለስ ተማሪዎችን መያዣ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ያነሱት ሃላፊው የከተማ አስተዳደሩ በተለይ የመምህራንን የቤት ጥያቄ ለመፍታት በቅርቡ መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል።

የአዲስአበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደበበ ወልደጻዲቅ የመምህራንን መብትና ጥቅማ ጥቅሞች ማስከበር ለትምህርት ጥራት ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ።

መምህራን የሚያገኙት ገቢ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የማይጣጣምና በቂ አለመሆኑንም ነው የሚያነሱት።

የመምህራን የኢኮኖሚ ጥያቄ በተለይ የቤት ኪራይ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2009 ዓም መምህራን የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ በተደረገው ጥረት 5 ሺህ መምህራን ቤት እንዲደርሳቸው መደረጉን አስታውሰው ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህ እርምጃ ባለመቀጠሉ አብዛኞቹ መምህራን ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ይናገራሉ።

በከተማዋ ከ15 ሺህ በላይ መምህራን ቤት የሌላቸው ሲሆን ይህን ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና ከትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ጥያቄያቸው እንደሚመለስ ቃል ተገብቶላቸዋል ብለዋል።

ምንም እንኳን የኑሮ ውድነቱ ቢከብዳቸውም ከሚያገኙት ገቢ ላይ ተማሪዎችን የሚመግቡና የመማሪያ ቁሳቁሶችን የሚያሟሉ ምስጉን መምህራን እንዳሉ ሁሉ ሃላፊነት የማይሰማቸው እንደማይጠፉም የቢሮ ሃላፊውና ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የመምህራን ድምጽ በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪዎችና የአድማ ቅስቀሳዎች በማህበሩ የማይታወቅና ህጋዊ መሰረት የሌላው ነው ብለዋል።

አብዛኞቹን መምህራን የማይወክሉ የቅስቀሳና የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪዎች ህጋዊ እውቅና የሌላቸው በመሆኑ ተማሪዎች መጪውን ፈተና ተረጋግተው እንዲፈተኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስአበባ ከ20 ሺ በላይ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም