የፍቼ ጫምባላላ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

88

ሀዋሳ ግንቦት 15/2011 የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፍቼ ጫምባላላ በዓልን በድምቀት ለማክበት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የዘንድሮው የፍቼ ጫምባላላ በዓል በመጪው ግንቦት 22 እና 23 በሀዋሳ ከተማ ይከበራል።

የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ለጋዜጠኞች እንዳሉት የፍቼ ጫምባላላ ባህላዊ ስርዓቱና ልምድን ሳይለቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው።

በሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች በሚወሰን ቀን በየዓመቱ የሚከበረው የብሄሩ የዘመን መለወጫ በዓል ዘንድሮ ያለምንም ችግር ማክበር እንዲቻል በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የፍቼ ጫምባላላ በዓል በጣም በርካታ እሴቶች አሉት ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን የያዘ በዓል ነው በዚህ መነሻ በዚህ በዓል አከባበር ወቅትም እነዚህ እሴቶች ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ አስፈላጊ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

 በበዓሉ ዝግጅት ዙሪያ በዞኑ ሁሉም ቀበሌዎችና በትምህርት ተቋማት ከህዝብ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በበዓሉ ዙሪያ ተከፍቶ የነበረው ዘመቻ ተገቢ አለመሆኑን ያስታወሱት አቶ ጃጎ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊና የአለም ቅርስ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደአምናው ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ከዞኑ ወጣቶች ጋር የተለያዩ ተግባራት እንደተከናወኑና ከበዓሉ አስቀድሞ ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ የመምሪያ ኃላፊ አመልክተዋል።

የፍቼ ጫምባላላ በዓል ዘንድሮ በዋዜማው የባህል ሲምፖዚየም እና ግንቦት 23 ደግሞ  በጉዱማሌ የዘመን መለወጫ በዓሉ እንደሚከበር ጠቁመው "በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለሁለት ሳምንት በተለያየ ስርዓት ይቀጥላል "ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ አካባቢ ነዋሪ ወጣቶች  እንደገለጹት የዘንድሮው የፍቼ ጫምባላላ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንደሚከበር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

ከወጣቶቹ መካከል የአላሙራ ቀበሌ ነዋሪ  ዘገየ ወጤ በሰጠው አስተያየት የዘንድሮ በዓል በህጋዊ መንገድ ባህሉ በሚፈቅደው ስርዓት መሰረት ያለጸጥታ ችግር ለማክበር እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግሯል።

ወጣት አስራት ከበደ በበኩሉ  የፍቼ ጫምባላላን በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም