ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያላቸውን መልካም ምኞት ገለፁ

82

ግንቦት 14/2011ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅዱስ ሲኖዶስ የጉባኤ አዳራሽ በመገኘት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት ከዚሀ ቀደም የነበረውን ታሪክ የቀየረ ነው ብለዋል።

“አባቶች ወደ ባለ ሥልጣናት ይሄዱ ነበር እንጂ መሪዎች ወደ አባቶች መምጣት ቀርቶ ነበር” ያሉት ፓትሪያሪኩ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ አንድነትና ከ42 ዓመት በኋላ ለተመለሱት የ4 ኪሎ ሕንፃዎች በጉባኤው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሲኖዶሱ ጉባኤ ባስተላለፉት መልእክትም ቤተ ክህነት ጠንካራ፣ ከሙስና የጸዳ፣ ግልጽነት ያለው ተቋምያለመሆናቸው ካህናትና ምእመናን ፍትሕ ፍለጋ በየመንግሥት ተቋማቱ መንከራተታቸው አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ችግር በመቅረፍ ምበየደረጃው ካሉ የመስተዳድር አካላት ጋር በመሆን ሕዝቡን ስለሰላም ፣ፍቅርና ዕርቅ እንድያስተምሩም አደራ ብለዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በመሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የእርዳታ ተቋማትን፣ የአካል ጉዳተኞች መርጃዎችን እንዲያቋቁሙ ጠይቀዋል፡፡

ሕዝቡ ለበዓል ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ለመሳለም ይሄዳልና ሕዝቡን ለማቀራረብ ፣ ለማገናኘትና አንድ ለማድረግ ብትሰሩ መልካም ነው ብሏቸዋል።

በረመዳን ጾም የመጨረሸዎቹ ቀናት ሕዝበ ክርስቲያኑ የተለመደዉን በጎ ተግባር መስጊዶችንና አካባቢውን በማጽዳት አንድነታችንን እናሳይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በክረምት በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ለመትከል አስበናልና አባቶች ሕዝቡን ብታስተባብሩ የሚል አደራም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም