የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር ትውውቅ አደረጉ

215

ግንቦት 14/2011  አዲሱ  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ  አንዳርጋቸው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የዲፕሎማቲክ  ማህበረሰብ አባላት ጋር ትውውቅ  አድርገዋል።

በትውውቁ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ትብብር እና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እየሰራች ያለውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሚኒስትሩ ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ 28ኛው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር  የሆኑት  አቶ ገዱ  የውጪ  ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው  ከተሾሙ በኋላ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተገናኝተው ሲወያዩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

በትውውቅ ፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም በኢትዮጵያ  በአሁኑ  ሰዓት  እየተወሰዱ ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች አብራርተዋል።

በዚህም እየተደረጉ ያሉ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎችን ያነሱ ሲሆን ለአብነትም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ከአገር ውጪ የነበሩ የተቃዋሚ ጎራ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መመለስን የመሳሰሉትየለውጡ ስኬቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

እየተደረጉ ካሉ ማሻሻያዎች የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት አካታች የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል እድል እየፈጠረ ያሉ መሆኑን ጠቅሰው የምርጫ ቦርድንና የፍትህ ተቋመት ላይ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።

እየተካሄዱ ካሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከልም ለግል ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና የውጪ ጉደይ ፖሊሲ ላይ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረትና ሰላም እና ደህንነትን ለማስፈን እየተሰራ ያለውን ሥራ  እንዲሁ የጠቆሙ ሲሆን ይህን ለማጠናከርም በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ለውጥ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናዊ የኢኮኖሚ እድገት ጭምር አስተጽኦፆ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነትና የደቡብ ሱዳን ሰላም ጠንካራና የተረጋጋ ቀጠናዊ ትስስር የመገንባት ህልምን  እውን በማድረግ  ተስፋ  የጫረ  ነው  ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ትብብር እና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እየሰራችው ያለውን ሥራም አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል።

ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላቱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበውና በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ድጋፍ ስለቸረውም አመስግነው ሚኒስቴራቸውም ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም ጭምር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም