ከ7ሺህ 600 በላይ ተፈናቃይ ተማሪዎች ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን አይወስዱም- የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

139

ግንቦት 14/2011 በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተከስቶ በነበረ ግጭት መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ከ7ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ዘንድሮ የሚሰጡትን ክልላዊና አገር አቀፍ ፈተናዎች እንደማይወስዱ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኖቹ በነበረው ግጭት  በ53 የአንደኛና በአምስት የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ተቋርጦ ቆይቷል ።

"በግጭቱ ተማሪዎቹን ጨምሮ የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ አባላት በመፈናቀላቸውና ተማሪዎች በቶሎ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሊመለሱ ባለመቻላቸው  ፈተናዎቹን እንዳይወስዱ ተወስኗል" ብለዋል ።

ፈተናዎቹን የማይወስዱት ከ4ሺህ በላይ የስምንተኛ  ክፍል እንዲሁም  ከ3ሺህ 600 የሚበልጡት ደግሞ የአስረኛ  ክፍልና መሰናዶ ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ተማሪዎቹ በመጪው ዓመት ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለውና በቂ ዝግጅት አድርገው ፈተናዎቹን እንደሚወስዱ አመላክተዋል ።

እንደ ምክትል የቢሮው ኃላፊ ገለጻ ተማሪዎቹ  በመጪው ዓመት መደበኛ ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው ፈተናዎቹን እንዲወስዱ ለማስቻል ቢሮው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ነው ።

በክልሉ ከ804 ሺህ በላይ በላይ የስምንተኛ፣ የአስረኛና የመሰናዶ ተማሪዎች ክልላዊና ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተናዎች እንደሚወስዱ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም