''ሀዋሳን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ከተማ ለማድረግ በተሰማራንበት የንግድ መስክ ጠንክረን እንሰራለን''- ባለሃብቶች

92

ሀዋሳ ግንቦት 14 / 2011 ሀዋሳን ምቹ የኢንቨስትመንት ከተማ ለማድረግ በተሰማሩበት የንግድ መስክ ጠንክረው እንደሚሰሩ የከተማዋ ባለሀብቶች ገለጹ።

ለከተማዋ ባለሃብቶች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

በከተማዋ በህክምና ዘርፍ የተሰማሩት የሊያና ሄልዝ ኬር ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ግርማ አባቢ "ኃላፊነት በሚሰማው ባለሀብት አገር እንደምታድግ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያሳያል" ብለዋል። 

የከተማው አስተዳደሩ ከተማዋን በ2020 ለኑሮ ምቹና ተመራጭ ለማድረግ የያዘውን እቅድ ለማሳካት በተሰማሩበት በጤናው ዘርፍ ቱሪዝም ቀዳሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

"የአካባቢው ባለሀብት የበለጠ ሲተጋ የውጭውን ባለሀብት የመሳብ አቅም አለው" ያሉት ዶክተር ግርማ፣ ባለሃብቶች ተግዳሮቶችን በመቋቋም የከተማዋ አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

በትምህርት ዘርፍ በነበራቸው ተሳትፎ እውቅና ያገኙትና ከዩኒክ ስታር ኮሌጅ የመጡት አቶ መላኩ አበራ በበኩላቸው አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የኢንቨስትመንት ሳምንት ሥራቸውን ያስተዋወቁበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

እሳቸውን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉ የከተማዋ ባለሀብቶች ባከናወኑት ተግባርም ከተማዋ አንደኛ መውጣቷ ለሥራ እንዳነሳሳቸው አስታውቀዋል፡፡
በተሰማሩበት የትምህርት ዘርፍ ጠንክሮ በመሥራት ከተማዋ ያላትን የኢንቨስትመን አማራጮች ማስተዋወቅና ተመራጭ እንድትሆን በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

የወዳደቁ ወረቀቶችን መልሶ በመጠቀም የመጸዳጃ ወረቀት(ሶፍት) የሚያመርተው የዛክ ሶፍት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰናይት ዳኜ በበኩላቸው መድረኩ ልምድ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል። 

የከተማው አስተዳደሩ በሰጣቸው እውቅና መደሰታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም ከአስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ለከተማዋ እድገት ድርሻዬን አወጣለሁ ብለዋል። 
"ሀዋሳን አሁን በተያዘው ፍጥነት ማሳደግ ከቻልን በ2020 እንደ ዱባይ ከተማ ተመራጭ የማድረጉ ራዕይ ይሳክል የሚል እምነት አለኝ" ሲሉም ተናግረዋል።
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ ኢንቨስትመንት ለከተሞች እድገት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አመልክተው፣ራዕይዋንለማሳካት በውሃ ዳርቻዎች፣ በትራንስፖርት፣ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታና በቱሪዝም ዘርፎች ያለውን ሃብት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ኢንቨስትመንት ገበያና ሰላምን ይፈልጋል" ያሉት አቶ ስኳሬ፣ የከተማዋ ባለሀብቶች ለከተማዋ ሰላም በህብረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
በአገር አቀፉ የኢንቨስትመንት ሳምንት የተሳተፉ ከ16 የሚበልጡ ባለሀብቶች እውቅና ሽልማት ያገኙ ሲሆን፣ ሥራውን የሚያግዙ ተቋማት የሽልማቱ አካል ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም