የጋምቤላ ክልል ለልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን ወጣቶች አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገነዘቡ

74

ጋምቤላ ግንቦት 14 /2011 የጋምቤላ ክልል ወጣቶች አንድነታቸውን በማጠናከር ለልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑሞድ ዑጁሉ አሳሰቡ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋምቤላ ከተማ ወጣቶች ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ዑሞድ ዑጁሉ በዚሀ ወቅት እንደተናገሩት ወጣቱ ትውልድ የመቻቻል፣የአንድነትና የአብሮነትን እሴቶችን በማዳበር ለክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን የሚያደርገውን ጥረት ሊያጠናክር ይገባል፡፡

በተለይም ወጣቱ ብዝሃነትን በመቀበል በክልሉ ብሎ በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ዋነኛው መሣሪያ መቻቻልና አብሮነትን ማጠናከር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡

የክልሉን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዑሞድ፣ ለቀጣይነት የሀሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ልምድ መዳበር አለበት ብለዋል፡፡

በተለይም በመካከላችን ያለውን የብሔር፣የሀይማኖትና ሌሎችም ልዩነቶች እንደ ውበት በመውሰድ የመቻቻልና የመከባበር እሴትን ማዳበር ለክልሉ ብሎም ለአገር ልማት  መሥራት እንደሚያሻ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ከሚለቀቅ ሐሰተኛ መረጃ ራሱን በመጠበቅና ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን በመያዝ ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ ጥረቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የወጣቱን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡        

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ኮንግ ጋትቤል በሰጠው አስተያየት የሰላም መኖር የእለት ተዕለት ተግባር ለመከወንም ሆነ ለክልሉ ልማት መረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡

በመሆኑም የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡

ሌላው ተሳታፊ ወጣት ኡጁሉ ኡጁሉ በበኩሉ በክልሉ ሰላምና አንድነትን ማጠናከርና ወጣቱ ችግሮች በጋራ ለመፍታት መሥራት እንዳለበት አመልክቷል፡፡

"በመካከላችን ያሉትን ልዩነቶች ተቻችለን አንድነታችንን በማጠናከር ለክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደር የበኩላችንን እናደርጋለን" ያለው ደግሞ ሌላ ወጣት ኡቦንግ ኡጉታ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከከተማዋ ከአምስቱም ቀበሌዎች የተወጣጡ ከ250 በላይ ወጣቶች ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም