በባንክ የክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ መድሃኒት በወቅቱ ከወደብ እየተነሳ አይደለም--የመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ

66

ግንቦት 14/2011 በአሰራር ችግር ሞጆ ወደብ ላይ መድሃኒቶች ለበርካታ ወራት እንደሚቆዩ የኢትዮጰያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ንግድ በባንክ ባለው የክፍያ መዘግየት  ጋር ተያይዞ መድሃኒት በሚያዝለት የጊዜ ገደብ ከወደብ እየተነሳ አይደለም።

በዚህም ሳቢያ መድሃኒቶች ለአቧራና ለጸሃይ በመጋለጣቸው የመፈወሻ ጊዜያቸውን እንዲያጥር ከማድረጉም በላይ ለህብረተሰቡ በሚፈለገው ወቅት መድሃኒት ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁመዋል።

በአማካይ ከ300 እስከ 400 ኮንቴይነሮች ከሁለት እስከ ሶስት ወር ወደብ ላይ የሚቆዩ ሲሆን አንድ አመት ያስቆጠሩም ኮንቴይነሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ለመድሃኒትና ለህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት የሚፈለገው የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ እንዲሰጥ መንግስት ቢፈቅድም የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ከፍያውን ባለመፈጸሙ መዘግየት እያጋጠመ እንደሆነ ተናግረዋል።

አንድ መድሃኒት ከውጭ ገብቶ ከ17 ቀን ላልበለጠ ጊዜ ከወደብ መነሳት እንዳለበት ቢታወቀም ኮንቴይነሮቹ ባለመነሳታቸው በወደብ ኪራይ  መንግስት አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ እየተዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም