የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ከሚጠበቅባቸው በታች መድሃኒት እያቀረቡ ነው

147

አዲስ አበባ ግንቦት 14/ 2011 የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ከሚጠበቅባቸው በታች መድሃኒት እንደሚያቀርቡ ተገለጸ።

የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ከሚጠበቅባቸው በታች  መድሃኒት ማቅረባቸው ተገለጸ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች የሚጠበቅባቸውን ያህል መድሃኒት ለህብረተሰቡ እያቀረቡ አለመሆኑን የኢትዮጰያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ይህን ያለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ነው።

 የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎኮ አብርሃም  በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአገሪቷ 13 የመድሃኒት ፋብሪካዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ምርት እየሰጡ አይደለም።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፋብሪካዎቹ ማቅረብ ከነበረባቸው መድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች ውስጥ 33 በመቶውን ብቻ ማቅረብ እንደቻሉ ነው የተናገሩት።

 በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ መድሃኒቶች ላይ እጥረት እንዲፈጠር፣ አገሪቷ ከውጭ በምታስገባው ምርት የምታጣውን ገንዘብ ማዳን አለመቻልና ዘርፉ ለመልካም አስተዳደር ችግር እንዲጋለጥ ማድረጉን አስቀምጠዋል።

ለፋብሪካዎቹ ውጤታማነት ማነስ እንደ ተግዳሮች ከተነሱት ውስጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የተቋማቱ የማስፈጸም አቅም ውስንነትና የተመረቱ መድሃኒቶች አለ አግባብ ለግሉ እየተላላፉ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በቀጣይ የፋብሪካዎቹን የማምረት አቅማቸውን የሚከታተልና ለመልካም እስተዳደር ችግሮች እንዳይጋለጡ የሚያደርግና ተጠያቂነትን የሚያሰፈን አሰራር ለመዘርጋት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግሯል።  

ፋብሪካዎቹ የሚፈለግባቸውን ሚና እንዲወጡና የህብረተሰቡን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ እንዲያሟሉ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደረግ ይገባልም ብለዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ ለሚከሰቱ የመድሃኒት እጥረት መንስኤዎች በጤና ተቋማት የመረጃ ልውውጥ አለመኖርና የአሰራር ክፍተት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የጤና ተቋማት ለኤጀንሲ የሚያቀርቡት የመድሃኒት ፍላጎት በጥናት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ የአቅርቦት አለመጣጣምም ይገጥማል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ኤጀንስው ባለፉት ዘጠኝ ወራት አሰራሩን ለማዘመንና ብልሹ አሰራሮችን ለመግታት በሰራተኛው መካካል የተሻለ መግባባት እንዲኖር በማድረግና ለመጋዘን የሚወጣውን ኪራይ ለማስቀረት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማትንና የፋብሪካዎችን የተጠያቂነት መንፈስ ለማረጋገጥ፣አሰራሩን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረትና የህብረተሰቡን የመድሃኒት ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥርት ግን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁሟል።

በአገሪቷ የህይወት አድንና የመሰረታዊ መድሃኒቶች ሽፋን 80 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱንና የ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ግዥ ቢፈጸምም የአቅርቦት ችግር እንዳለ ተናግረዋል።

ይህንን ለመፍታትም ተቋሙ የመድሃኒት አቀርቦቱን እስከታችኛው የሀብረተሰብ ከፍል አስኪደረስ ክትትል ማድረግ አለበት ተብለዋል።