ፖሊስ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አገራዊ ለውጡን ማጠናከር ይጠበቅበታል - ምከትል ከንቲባ መሃዲ ጊሬ

42

ድሬዳዋ ግንቦት 14/ 2011 የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አገራዊ ለውጡን ለማጠናከር መሥራት እንደሚጠበቅበት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አስገነዘቡ።
ለፖሊስ አባላትና አመራሮች ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና በጅግጅጋ እየተሰጠ ነው፡፡

ምክትል ከንቲባ መሃዲ ጊሬ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሳሰቡትፖሊስ አገራዊና ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትናሙያዊ ብቃቱን በሚያጠናከር መንገድ መንቀሳቀስ አለበት፡፡

በተለይ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ የህዝብ አመኔታ ለማግኘት መትጋት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

በተለይ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ለህዝቡ የሚያረካ ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት መሥራት እንዳለባቸው አቶ መሃዲ አሳስበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ በበኩላቸው ሥልጠናው ፖሊስ የሕዝብ አገልጋይ በመሆን በአደረጃጀት፣በአሠራርና በአመለካከት በመታገዝ አገራዊ ለውጡን ለማራመድ  እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው ፖሊስን በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር በማነጽሕዝቡን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ፖሊስ ህዝቡን በእኩልነት በማገልገል ለአገሩ ክብር ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ፖሊስ ከየትኛውም አቅጣጫ ሊጎትተው ከሚፈለገው አመለካከት በመራቅ፤ ለጎሳና ለኃይማኖት ጫና ሳይገዛ ህዝቡን በፍትሃዊነት የማገልገል ኃላፊነቱን እንዲወጣ  አስገንዝበዋል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች  መካከል አቶ ሐሰን ሽፋ ከሥልጠናው በኃላ ፖሊስ ህዝቡን በፍትሃዊነትና በእኩልነት የማገልገል ሙያዊ ሥነምግባሩን ይወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርገለሁ ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ይመኙሻል ማስረሻ የተባሉ ነዋሪ በአንዳንድ የፖሊስ አባላት ላይ የሚታዩን ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ሥልጠናው እንደሚያግዝ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣት ኢማን ዓሊ በበኩሉ ስልጠናውበጥልና በድብድብ ውስጥ በመግባት ሁከት የሚፈጥሩ አንዳንድ ፖሊሶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያግዛቸው ብዬ አምናለሁ ብሏል፡፡

ለፖሊስ የሚሰጠው ሥልጠና ፖሊስና ህዝብ በደንብ ተቀናጅተው ሠላምና ፀጥታቸውን በጋራ ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸውተስፋቸውን  የገለጡት ወይዘሮ ሩቂያ አህመድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም