በመስኖ እየለማ ያለው የቆላ ስንዴ አበረታች ውጤት ታይቶበታል

204

ግንቦት 14/2011  የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር የተገኙ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በመስኖ የማምረት ስራውን እያስፋፋ መሆኑን አስታወቀ።

ማዕከሉ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለመተካት የምርት ስራውን ወደ አንድ መቶ ሺህ ሔክታር መሬት ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ ይገኛል።

በማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪና የስራ ሒደቱ ባለቤት አቶ አደም ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ በሙከራ ደረጃ በአንዲት ሴት አርብቶ አደር ሶስት ሔክታር ማሳ ላይ ማምረት የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው ።

የምርምር ማዕከሉ 8 የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ወደ ሰርቶ ማሳያ ስራ ሲሸጋገር አይቻልም የሚል ሀሳብ ሲነሳበት የነበረ ቢሆንም በአርብቶ አደሯ ማሳ ላይ በተደረገው ሙከራ በሔክታር በአማካይ 34 ኩንታል ምርት በመገኘቱ መነቃቃት መፍጠሩን ተመራማሪው አስረድተዋል ።

“በቆላማው የአፋር ክልልና በኦሮሚያ የማላመድ ስራ በማከናወን አምና በ700 ሔክታር መሬት ላይ በመስኖ በማልማት ከደጋው አካባቢ የማይተናነስ ምርት በመገኘቱ ዘንድሮ በ3ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ ተዘርቶ ምርቱ እየተሰበሰበ ነው” ብለዋል ።

በቆላ ስንዴ የመስኖ ልማት ላይ የታየውን አንፀባራቂ ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየቱ በሚቀጥለው ዓመት በአገሪቷ በሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች 100 ሺህ ሔክታር ለማልማት መታቀዱን ተመራማሪው አስታውቀዋል ።

የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራው በየዓመቱ በማስፋት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ለመላቀቅና ከተቻለም ወደ ውጭ መላክ የምንጀምርበት ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን የሚል ተስፋ ማሳደሩን አስረድተዋል ። 

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ለመስኖ ልማት አገልግሎት እንዲውሉ በምርምር ያወጣቸው ሰባት የዳቦና አንድ የፓስታና ማካሮኒ የቆላ ስንዴ ዝርያዎች ጋምቦ ፣ ሉሲ ፣ ወረር ፣ ፈንታሌ አንድ ፣ ፈንታሌ ሁለት ፣ አሚባራ አንድና አሚባራ ሁለት የሚል ስያሜ ተሰጥቶአቸዋል ።

የቆላ ስንዴ ዝሪያዎቹ በጥቅምት ወር አጋማሽ ተዘርተው ከ80 እስከ 90 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን ባለሙያው ተናግረዋል ። 

የቆላ ስንዴው አሁን በመስኖ የሚለማባቸው አካባቢዎች አንዳንዱ ስንዴ በእርዳታ ካልሆነ በስተቀር እንዴት እንደሚመረት በማያውቁ አርብቶ አደሮች አካባቢ መሆኑንም ከተመራማሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

አቶ አህመድ አህመድ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ በወረር አካባቢ የባዳሃሞ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በአካባቢው ስንዴ በመስኖ ሲለማ አይተው አያውቁም ነበር ።

አምና ከወረር ግብርና ምርምር ማእከል የማዳበሪያ ፣ የዘርና የባለሙያ እገዛ አግኝተው በ34 ሔክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ በማልማት በሔክታር በአማካይ 37 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችለዋል ።

በአምናው ስኬት በመነሳሳት ዘንድሮ በ260 ሔክታር መሬት ላይ ያለሙትን የቆላ ስንዴ በአጭዶ መውቂያ ኮምባይነር ምርታቸውን በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ ።

ዘንድሮ በሔክታር የሚያገኙት ምርት ከአምናው የተሻለ እንደሚሆን እየተሰበሰበ ካለው ምርት መረዳት እንደቻሉም ገልፀዋል ።

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አቶ አህመድ አምና ያመረቱትን ስንዴ አዋጭነቱን ለማወቅ በሰራው ሒሳብ ወጪውን ሁሉ ሸፍኖ 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘታቸውን አረጋግጧል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ፈቴሌዲ ቀበሌ ነዋሪዎች በታሪካቸው የቆላ ስንዴን በመስኖ ሲለማ ያዩት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ። 

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብዶ ኒኒ በሰጡት አስተያየት በግብርና ምርምር ድጋፍ 1ነጥብ 5 ሔክታር መሬት በቆላ ስንዴ እንዲሸፈን አድርገዋል ።

በማሳ ላይ እየታየ ያለው ሰብል ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልፀው ልማቱን የበለጠ ለማጠናከር ሁሉም የመንግስት አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት ጠይቀዋል ።

አቶ ሙሳ ዱቤ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ለጊዜው በ1 ሔክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ ማካሄድ መጀመራቸውን ገልፀው የደረሰው ሰብል ወፍ እያጠፋው በመሆኑ ለወደፊቱ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ጠቁመዋል ።