በጋምቤላ በመፈተኛ ክፍል ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት የተገኙ 27 ተንቀሳቃሽ ስልኮች ተያዙ

67
ጋምቤላ ግንቦት 29/2010 በጋምቤላ ከፍተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት እየተሰጠ ባለው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለኩረጃ ተግባር ለማዋል የተዘጋጁ 27 ተንቀሳቃሽ ስልኮች  መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ሞባይሎቹን መያዝ የተቻለው  ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ክፍሎች ከመግባታቸው በፊት በተካሄደው ፍተሻ ነው። የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት  ባልደረባ ዋና ኢንስፔክተር ዋንጫ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደገለጹት  ሞባይሎቹ  የፈተና ጸጥታ አስከባሪዎች ወደ ፈተና ጣቢያው ከመድረሳቸው በፊት ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች  ለኩረጃ ተግባር ወደ መፈተኛ ክፍሎች እንዳስገቧቸው ይገመታል፡፡ በአሁኑ ወቅት  ሞባይሎቹ  ፖሊስ በእግዚበትነት በመያዝ  የማን እንደሆኑ  እያጣራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከሞባይሎቹ ውስጥ እስካሁን የባለቤትነት ጥያቄ እንዳልቀረበ ጠቁመው ፖሊስ በቀጣይም ይህን መሰል ወንጀል የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በጋምቤላ ክልል ባለፈው ሳምንት በተሰጠው ሀገር አቀፍ የ10ኛ ክፍል ፈተና በሁለት የመፈተኛ ጣቢያዎች ሰባት ግለሰቦች ለሌላ ተማሪ ሲፈተኑ መያዛቸው በወቅቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም