የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለ7 ሺህ 29 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

117

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2011የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በልዩ ልዩ ወንጀሎች በመሳተፍ በህግ ጥላ ስር ላሉ 7 ሺህ 29 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።

ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ዘሬ በሰጡት መግለጫ የክልሉ ህገ  መንግስት  አንቀጽ 57/1 ለፕሬዚዳንቱ በሚሰጠው ስልጣን መሰረት በክልሉ የተለያዩ  ወንጀሎችን ፈጽመው በህግ ጥላ ስር ላሉ 7 ሺህ 29 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

በህጉ መሰረት ጥናት ተደርጎና ይህን የሚያጣራ ቡድን ለፕሬዚዳንቱ አቅርቦ በተወሰነው  ውሳኔ መሰረት በቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ያሳዩና በጥፋታቸው የተጸጸቱት ናቸው ይቅርታ የተደረገላቸው።

ከዚህ ውጭ ይቅርታው የማይመለከታቸው ታራሚዎች በህጻናትና ሴቶች ላይ ወንጀል የፈጸሙ፣ በዘር ማጥፋት የተከሰሱ፣ በደን መመንጠር የተከሰሱ፣ በህገ ወጥ ንግድና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች የተሳተፉ የህግ ታራሚዎች ናቸው።

እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለጻ የህግ ታራሚዎቹ ወደ ህዝቡ ሲቀላቀሉም መልሶ በቂም በቀል ጉዳት እንዳይደርስባቸው በባላህዊው መንገድ የእርቅ ስነ ስርዓት የሚፈጸም ይሆናልም ተብሏል።

የታራሚዎች ቤተሰቦችና ህብረተሰቡም እነዚህን ታራሚዎች ተቀብሎና አቅፎ  ወደ  መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱም ሊረዷቸው ይገባል ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ   ተናግረዋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎችም በቆይታቸው በቀሰሙት ልዩ ልዩ ሙያዎች ሰርተውና ልማት ላይ ከልባቸው ተሳትፈው ህይወታቸውን እንዲቀይሩና ህብረተሰቡንም እንዲክሱ አቶ ሽመልስ አሳስበዋል።

ይቅርታ ለተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ መንግስታቸው ለወደፊቱም ወንጀልና ወንጀለኛን በሚቀንሱ ተግባራት ላይ ጠንክሮ እንደሚሰራና ወንጀልን በመከላከሉ ስራም ህብረተሰቡ ከጎናቸው እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም