የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ላይ ሊደረግ የነበረው ውይይት ተራዘመ

65

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2011 የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ላይ ሊደረግ የነበረው ውይይት ቁልፍ የሚባሉ የክልል ባለድርሻ አካላት ባለመገኘታቸው ምክንያት ወደ ሌላ ቀን ተራዘመ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 'የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ' በሚመለከት ከክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ለዛሬ ቀነ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።

የውይይቱ ዓላማም ረቂቁ አዋጅሆኖ ከመውጣቱ በፊት ከቁልፍ ባለድርሻና አስፈጻሚ አካላት ግብዓት መሰብሰብ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት፤ ኮሚቴው የሚመለከታቸው አካላት በውይይቱ እንዲገኙ በመገናኛ ብዙኃን  ማስታወቂያ ከማስነገር በተጨማሪ ደብዳቤ ተደራሽ አድርጓል።

"ይሁንና ለውይይቱ የተገኙ ባለድርሻ አካላት እጅግ ጥቂት በመሆናቸው ምክንያት ውይይቱ ለቀጣይ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተራዝሟል" ብለዋል።

 ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በእለቱ በመገኘት የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉም ሰብሳቢው ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል አስተዳዳርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ዛሬ ከተገኙት ጥቂት ባለድርሻ አካላት መካከል ይገኙበታል።

'የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ሚያዚያ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ለተጨማሪ ዝርዝር እይታ በዋነኝነት ለውጪ ጉዳይና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በረዳትነት ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል።

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የአገርንና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን እና የህዝቦችን መብትና ደህንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተዘጋጀ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም