ከንግዱ ማህበረሰብ ለልማት የሚያግዝ 300 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው

64

መቀሌ ግንቦት 14/2011  የግንቦት 20 በዓልን አስመልክቶ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለልማት የሚያግዝ 300 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትግራይ ክልል ንግድ ማህበረሰብ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው አባል አቶ አሸናፊ ኃይሉ ትላንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ከዝግጅቱመካከል  በመጪው ዓርብ በመቀሌ ከተማ የሚጀመረው  የገንዘብ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን አንዱ  ነውበዚህም በከተማው ከሚገኙ ነጋዴዎች 150 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።

በከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች በቴሌቶኑ እንደየአቅማቸው ድጋፍ በማድረግ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራትና ግንባታቸው የተቋረጡ የመሰረተ ልማት አውታሮች ለማጠናቀቅ እንዲያግዙ  ጠይቀዋል።

የኮሚቴው አባል አቶ አሰፋ ገብረስላሴ በበኩላቸው አሁን ለተገኘው ሰላምና ልማት የግንቦት 20 ድል  አይነተኛ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

"28ኛው የግንቦት 20 የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ካገኘነው ገቢ ቀንሰን ለክልላችን ልማት በማዋል ልናከብረው ይገባል" ብለዋል።

ከክልሉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት መካከል ወጣት ፍጹም አስገዶም በሰጠው አስተያየት በገንዘብ እጥረት ምክንያት የተቋረጡ የልማት ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል ለማጠናቀቅ በሀገር  ውስጥና በውጭ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችና ደጋፊዎች እንዲያግዙ ጠይቋል።

"የመንግስት ጥሪ ሳንጠብቅ ለመሰብሰብ የታቀደውን 300 ሚሊዮን ብር በግንቦት ወር ውስጥ እንሰበስባለን" ያለው ወጣት ፍጹም የሚቀጥለውን ዓመት ጨምሮ አንድ ቢሊዮን ብር ከንግዱ ማህበረሰብ ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም