ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ ስለ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጡ

56
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ ላይ ማብራሪያ ሰጡ፡፡ የአገራችንን ኢኮኖሚያዊ እድገት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም የተሻለ የወጭ ንግድ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ከአሁኑ የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያመነበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ መወሰኑን ወ/ሮ ሂሩት በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ መወሰኑን አብራርተዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪ ማስተላለፉንም ገልጸዋል። ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት በአልጀርስ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ መፈጠሩን በማስታወስ በአሁኑ ጊዜ ሀገራቱ የዕውነት ሰላም እንዲያሰፍኑ ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል ወ/ሮ ሂሩት፡፡ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት የኢትዮጵያና ኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መኖሩ ጠቃሚ መሆኑን በመጥቀስ ይህንን ባለማድረጋችን በሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ብዙ ዕድሎችን አጥተናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳስርን ህዝቦች በመሆናችን ለሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ለመተግበር መወሰኑን ወይዘሮ ሒሩት ገልጸዋል፡፡ የወ/ሮ ሂሩትን ማብራሪያ ተከትሎ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ አባላት ኢትዮጵያ የወሰደችውን እርምጃ የሚደነቅና እሰየው የሚያስብል መሆኑን አስተያየት የሰጡ ሲሆን ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም