በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ

50

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011 በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰራተኞች ላይ ዐቃቤ ህግ ዛሬ ክስ መሰረተባቸው። 

የዐቃቤህግ ክስ የተመሰረተባቸው 1ኛ ኃይለስላሴ ቢሆን፣ 2ኛ የማነብርሃን ታደሰ ፣ 3ኛ ሙከሚል አብደላ ፣ 4ኛ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴን  ያልተያዙ/5ኛ ያሬድ ይገዙ፣ 6ኛ አንዳርጋቸው ሞግሪያ /ያልተያዘ/ እና 7ኛ ያለው ሞላ ናቸው።

ዐቃቤህጉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1ሀ እና 411/1/ ሐ እና 2 ላይ የተመለከተውን በመተላለፋቸው ነው ክስ የመሰረተባቸው።

ተከሳሾች በኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ሲሰሩ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት ተጠቅመው ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባውን የመንግስትና የህዝብ ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ተከሰዋል።

  3ኛ ተከሳሽ የፌዴራል መንግስት ግዢ አፈፃፀም መመሪያ አንቀፅ 25 ንዑስ አንቀፅ 9 ነና 10 መሰረት ምንም ድርድር ሳይደረግ ሲትረስ ኢንተርናሽናል /citrus international/ ከተባለ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ስምምነት በማድረግ ግዢ እንዲፈጸም ያደረጉ መሆኑን የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።

በአጠቃላይ ተከሳሾች የመንግስትና የህዝብን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የመድኃኒት ግዢ መፈፀም እያለባቸው ይህን በማያስጠብቅ ሁኔታና ህግን ባልተከተለ መልኩ ግዢ እንዲፈጸም በማድረጋቸው በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በአቶ ሃይለስላሴ ቢሆን የክስ መዝገብ አቶ የማነብርሃን ታደሰ፣ አቶ ሙከሚል አብደላ፣ወይዘሮ ሳፊያ ኑርና አቶ ማስርሻ አሰፋ ላይ ተጨማሪ ክስ መስርቷል።

የክስ መዝገቡ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ ከ313 ሺህ ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነው።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ክሱ የዋስትና መብት የማያስከለክልና ቀላል ጉዳት በመሆኑ ደበኞቻቸው በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በበኩሉ ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብትን የሚከለክል በመሆኑ ጥያቄውን ውድቅ ያደረገው ሲሆን ጉዳቱን በተመለከተ ማስረጃ በሚቀርብበት ወቅት የሚታይ ይሆናል ብሏል።

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ በሁለቱም መዝገብ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰው ተከሳሾች የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም