ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ማኅበራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መንግስት ይደግፋል---ኤጀንሲው

83
ደሴ ሚያዝያ 23/2010 ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ችግርን ለመፍታት የኅብረት ስራ ማኅበራት እያደረጉት ያለውን እቅንቅስቃሴ ለማጠናከር መንግስት የሚደግፍ መሆኑን የፌዴራል ኅብረት ስራ ማኅበራት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡ ክልላዊ የኅብረት ስራ ማህበራት አውደ ርዕይ ፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት ማኅበራት የተለያዩ የግብርናና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ በሀገሪቱ ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እየሰሩ ነው፡፡ መንግሥት ማኅበራቱ የጀመሩትን መልካም እንቅስቃሴ ለማጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ያለው አውደ ርዕይ ፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ማኅበራቱን ለማጠናከር ከሚሰሩ ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዝግጅት ገጠሩን ከከተማ፣ አርሶ አደሩን ከሸማቹ በማገናኘት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የግብርናውን ዘርፍ ቀጣይ እድገት ለማረጋገጥና ዘርፉ እንዲዘምን ተመሳሳይ ዝግጅቶች እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል በበኩላቸው የኅብረት ስራ ማኅበራት ችግሮችን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል። ከመስሪያና ከመሸጫ ቦታዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ የማኅበራቱን ቅሬታ የክልሉ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለመፍታት የዞንና የከተማ አስተዳደሮች ኃላፊነት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ አውደ ርዕዩን ፣ ባዛሩንና ሲምፖዚየሙ ያዘጋጁት የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ስራ ማኅበራት ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽህፈት ቤቶች በጋራ መሆኑ ተገልጿል። ለአምስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ዝግጅት 87 የኅብረት ስራ ማኅበራት የተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የግብርና ምርቶች ለሸማቹ እያቀረቡ ናቸው፡፡ የገበያ አማራጭ ከመፍጠር ባሻገር ሸማቾች ለሚፈልጓቸው ምርቶች በበቂ መጠን መረጃ ማግኘት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም