የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች በጋራ የመኖር ባህላቸው እንዲጠናከር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

145

ዲላ - ግንቦት 13/2011 የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች በጋራ የመኖር ባህላቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሰብአዊ መብት ተሟጓቹ ታማኝ በየነ ጥሪ አቀረበ፡፡

ታማኝ በየነ በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ በመገኘት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በተመለከተበት ወቅት ነው ጥሪውን ያቀረበው።

በዚህ ወቅት  የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው መጠለያ ጣቢያዎች ተዘግተው በማየቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

በቀጣይም ዜጎች በዘላቂነት ተቋቁመው እራሳቸውን ችለው  እንደቀድሞው ሁሉም በልማቱ ግንባር ቀደም ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው አመልክቷል።

" የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ አንድ ህዝቦች ናቸው "ያለው ታማኝ በየነ አብሮ የመኖር ነባር ባህላቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።

በስፍራው የተገኙት የሰላም  ሚኒስትር ዲኤታ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው ዜጎች ወደቄያቸው መመለሳቸውን ተከትሎ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ለመጣው ለውጥ መንግስትና ህዝብ በጋራ ካደረጉት ጥረት ጎን ለጎን አጋር አካላትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዜጎች የቀደመ ኑሮቸውን እስኪጀምሩ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወዘሪት የምስራች ገመደ በበኩላቸው ተፋናቃይ ዜጎቹ መንግስትና ህዝብ በጋራ ባደረጉት ጥረት ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተፈናቃሉ ዜጎችን ለመደገፍ ያሳዩትን ወገንተኝነት በተለይም ግሎባል አሊያንስ በሚባለው ድርጅት በኩል ታማኝ በየነ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአካባቢው አመራሮች፣ የሃገር ሽማሌዎችና ሌሎችም ነዋሪዎች ለታማኝ በየነ አቀባበል አድርገውለታል፡፡

ከጌዴኦና ጉጂ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ታማኝ በየነ በግሎባል አሊያንስ በኩል 31 ሚሊየን ብር ለወርልድዲቪዥን ማስረከቡ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም