በአበርገሌ ወረዳ የተከሰተው የአተት በሽታ እንዳይስፋፋ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

29

ግንቦት 13/2011 በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ የተከሰተው የአተት በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይስፋፋ የሕክምና ቡድን ተደራጀቶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሳየ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው ከሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በደቢና ሳቃ ቀበሌዎች የአተት በሽታ ተከስቷል።

በእነዚህ ቀበሌዎች በበሽታው የተያዙ 67 ሰዎች በአቅራቢያው በተቋቋሙ ጊዜያዊ ጣቢያዎች ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደኃላፊው ገለጻ እስካሁን ድረስ በበሽታው ተይዘው ወደሕክምና ተቋም ያልመጡ አራት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

በደቢና ሳቃ ቀበሌዎች የተከሰተው የአተት በሽታ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመትም ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የተውጣጡ አባላትን ያቀፈ ሦስት የሕክምና ቡድን መደራጀቱን ነው አቶ አሳየ የተናገሩት።

በሕክምና ቡድኖቹ በጠቅላላው 14 የሕክምና ባለሙያዎች የሚገኙ ሲሆን ጤና ባለሙያዎቹም ወደቀበሌዎቹ ተሰማርተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከዕለት ወደ እለት የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ቢሆንም ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሳቃ ቀበሌ በሽታው እንደአዲስ መታየቱን አስታውቀዋል፡፡

“በዚህም አንዲት ሴት ልጅ በበሽታው ተጠቅታ ሕክምና ተቋም ሳትደርስ ሕይወቷ አልፏል፤ሌላ አንዲት ነፍሰ ጡር እናት በአሁኑ ወቅት በሕክምና ተቋም ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል” ብለዋል፡፡

በሽታው ወደ ሰሃላና ዝቋላ ወረዳዎች እንዳይዛመት በህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተማር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

“የተከሰተውን የአተት በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ እየተደረገ ነው” ያሉት ደግሞ የአበርገሌ ወረዳ ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎበዜ አዘዘው ናቸው፡፡

አተት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ቆላማ በመሆናቸውና የውሃ አመራጭ በቀላሉ የማይገኝባቸው በመሆኑ ህብረተሰቡ የተገኘውን የወንዝ ውሃ አክሞ እንዲጠቀሙ ከ115 ሺህ በላይ የውሃ አጋር እየተሰራጨ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም