ዩኒቨርሲቲው ምርታማነትን የሚያሳድግ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች ማሳ እያላመደ መሆኑን አስታወቀ

102

ግንቦት 14/2011 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ለምነትን በማሻሻል እስከ 60 በመቶ ምርታማነትን የሚያሳድግ  የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እያላመደ መሆኑን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የመሬት ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ትምህርት ክፍል አስተማሪና ተመራማሪ ዶክተር ካሳ ተካ እንዳሉት፣ ከትል የሚመረተውና ቨርሚንግ በመባል የሚታወቀው ኮምፖስት ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን በማሳደግ በኩል ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል።
ተቋሙ በምርምር ያገኘውን ይህን ማዳበሪያ በትግራይ ክልል ሦስት ወረዳዎች በተመረጡ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የማላመድ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።


የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም በምርምር ያገኙትን ውጤት በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎች የሚገኙ 96 ሴት አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ወደተግባር መቀየራቸውን አስታውሰዋል።


ዶክተር ካሳ እንዳሉት ቀያይ ትሎች ተረፈምርት ተጠቅመው የሚያወጡት ቨርሚንግ የተባለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) አርሶ አደሮቹ ከሚጠቀሙበት ፍግና ዘመናዊ ማዳበሪያ ጋር ሲነጻጸር በምርት ላይ 60 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተረጋግጧል። 

ኮምፖስቱ ማሳው እስከ 30 በመቶ የውሃ ስርገት እንዲኖር በማድረግና እርጥበትን በመያዝ ጠቀሜታ እንዳለው የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ማረጋገጣቸውን ዶክተር ካሳ ተናግረዋል።

ውጤቱን በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ይበልጥ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ካሳ ያስታወቁት።

ቨርሚንግ ኮምፖስት ትሎቹ በሚያመርቱት ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የበለፀገ በመሆኑ ተክሉ ከአፈሩ የሚያገኘውን ንጥረ ነገር እስከ ሰባት እጥፍ በመጨመር የተሻለ ምርት እንዲሰጥ ያግዛል ብለዋል። 

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በአፅቢወንበርታ ወረዳ የሩባፈለግ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር ፍሬወይኒ ተኽለ እንዳሉት፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ትሎችን በማራባት የሚያገኙትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው አፕልን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ገቢያቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸው ተናግረዋል።

“የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ትሎቹን ሲያመጡ ጠቀሜታ ያላቸው ስላልመሰለን ለመቀበል ተቸግረን ነበር “ ያሉት ወይዘሯዋ፣ ትሎቹ የሚያወጡትን ማዳበሪያ በ3ሺህ 500 ብር በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸው አስረድተዋል።

ከትሎቹ የሚያመርቱት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ያለውን ጥቅም በመረዳት ለመጪው ክረምት የሚጠቀሙበት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ከወዲሁ ማዘጋጀታቸውንም ወይዘሮ ፍሬወይኒ አመልክተዋል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ ዓዲቅሳንድድ ቀበሌ የሚኖሩት ሌላዋ ሴት አርሶ አደር ለተገብርኤል ረዳ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ግማሽ ጥማድ በሚሆነው ማሳቸው ላይ ጌሾ ቢተክሉም የተሻለ ምርት ለማግኘት ሳይችሉ መቆየታቸው አስታውሰዋል።

ከትሎቹ የሚገኘው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በተወሰኑ አትክልቶች ላይ ከጨመሩ በኋላ ልዩነነት ማየት እንደቻሉ የተናገሩት አርሶ አደሯዋ፣ ይህም ትሎቹን በስፋት ለማራባት ምክንያት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

በእዚሁ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ መድህን አሰፋ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በጓሮቸው ውስጥ ለሚገኙ 100 የጌሾ ተክሎች በቂ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ስለማይጠቀሙ የተሻለ ምርት ሳያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ቨርሚንግ ኮምፖስት መጠቀም ከጀመሩ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በጓሯቸው ካለው የጌሾ ተክል የሚያገኙትን ምርት በመሸጥ በሳምንት እስከ 300 ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም