የሐረር ከተማ የታክሲ አገልግሎት አሰጣጥ እንዳማረራቸው ተገልጋዮች ተናገሩ

70

ሐረርግንቦት 13/2011 የሐረር ከተማ የታክሲ አገልግሎት ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና በኮንትራት አገልግሎት አሰጣጥ መቸገራቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ። 
የሐረሪ ክልል ትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ህግ በማያከብሩት ላይ እርምጃ እየወሰድኩ  ነው ብሏል፡፡

የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ በተለይም ባለ ሦሰት እግር ታክሲዎች በመንግሥት የወጣውን ታሪፍ በመጋፋት ይሰራሉ።አገልግሎታቸውንም በኮንትራት የተገደበ አድርገዋል ይላሉ።

ከነዋሪዎቹ መካከል መምህር ዳንኤል አምሃ በከተማዋ ነዳጅ እጥረት ባለተከሰተበት ሁኔታ ታክሲዎቹ መንግሥት  ያወጣውን ታሪፍ በመጣስ ቀድሞ ከነበረው እጥፍ ክፍያ እንድንከፍል፤አገልግሎቱንም በኮንትራት እንድናገኝ ተገደናል ሲሉም ምሬታቸውን ገልጸዋል።

''የመንግሥት ሠራተኛው በቀን ለታክሲ አገልግሎት እስከ 30 ብር እየከፈለ ይገኛል። ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ እፈልጋለሁካለ፤ የሥራ ሰዓቱን አሳልፎ ይገባል። ይህም በሥራው ላይም ተፅእኖ እየፈጠረበት ነው። መንግሥት በዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል'' ሲሉ  አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ዓለማየሁ ተሰማ መንግሥት የታክሲ አገልግሎት ፈቃድ ቢሰጣቸውም ፤ በህጋዊ መንገድ እንደማይሰሩና ቁጥጥር እንደማይደረግባቸው ይገልጻሉ።

በተለይ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው  እንዲሰሩ ተገቢው ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል ባይ ናቸው።

የታክሲ አሽከርካሪው ወጣት ጸጋዬ አድማሱ በከተማው ባለው የቤንዚን እጥረት መንግሥት ከተመነው በእጥፍ ዋጋ ሥራቸውን እያከናወነ መሆኑን ይገልጻል።በዚህም ምክንያት ተሳፋሪዎችን በኮንትራትና ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ለመሥራት መገደዱን አስታውቋል።

የመለዋወጫ ዕቃዎችና  ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነትም ችግር በኑሮአቸው ላይ ችግር ስለፈጠረባቸው በታሪፉ በላይ ለማስከፈል እንደተገደደ ተናግሯል።
የሐረሪክልል ትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ ኃላፊ አቶ ያሲን ሽኩሪ  ጽህፈት ቤታቸው ታሪፉንን አክብረው በማይሰሩት ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ብሏል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት የመንገድ ደህንነት፣ቁጥጥርና ስምሪት ዳይሬክተር አቶ ጀማል አብዱላሂ ኅብረተሰቡ ቅሬታ ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሐረሪ ክልል ከ4ሺህ 400 የሚጠጉ ታክሲዎች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም