ኢዜማ በተሰኘው ፓርቲ 'ውህደት ሳንፈጽም እንደተዋሃድን ተደርጎ በፓርቲያችን ላይ ስም ማጥፋት ተፈጽሟል' - ሁለት ፓርቲዎች

66

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011 ኢዜማ በተሰኘው አዲስ ፓርቲ 'ውህደት ሳንፈጽም እንደተዋሃድን ተደርጎ በድርጅታችን ላይ ስም ማጥፋት ተፈጽሟል' ሲሉ በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ አቀረቡ።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የአዲስ ትውልድ ፓርቲና አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በግንቦት ሰባት ንቅናቄና ችግር በፈጠሩ የፖርቲያቸው አባላት ላይ "በህግ ተጠያቂ እናደርጋለን" ብለዋል።

በያዝነው ግንቦት መባቻ ላይ የኢትዮጵ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) የተሰኘ አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ መመስረቱ ይታወሳል።

ፓርቲው ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ተዋህደው መመስረቱን በይፋ ቢገልጽም፤ "ራሳቸውን አክስመው ተዋህደዋል" ከተባሉት ድርጅቶች መካከል አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)እና አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ግን "ራሳችንን አላከሰምንም፤ አልተዋሃድንም" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የአትፓ ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ታፈሰ ከሌሎች የፓርቲው አመራር አባላት ጋር በጋራ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አትፓ ከተመሰረተበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት በሰላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ።

ፓርቲው በርዕዮተ ዓለም ከሚመስሉት ሌሎች አቻ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅትና በጥምረት ለመስራት ውይይቶች እያደረገ መሆኑንም ገልጸው፤ ከግንቦት ሰባትና ሌሎች ፓርቲዎች ጋር" ውህደት ፈጽሟል" ተብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተገለጸው ግን "ከዕውነት የራቀ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው" ሲሉ አጣጥለዋል።

የፓርቲው ህግና ደንብ መሰረት የፓርቲው ማዕከላዊና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በሌለበት ፓርቲውን ከተቀላቀለ ሁለት ወር የሞላው አባል፣ እንዲሁም የፓርቲው መታወቂያ የሌለው አንድ ግለሰብ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው አትፓ ውህደት መፈፀሙን መግለጻቸው ትልቅ "የፖለቲካ ወንጀል ነው" ብለዋል።

ስለሆነም የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት አትፓ ከማንም ጋር ምንም አይነት ውህደት እንዳልፈጸመ እንዲገነዘቡ፣ ፓርቲው እንደተዋሃደ የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የአንድነት የፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ትግስቱ አወሉ በፓርቲው ስም በፊት የ'ቀድሞ' በሚል ቃል በመጨመር አንድነት ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንደፈጸመ ተደርጎ እንዲገመት "ፖለቲካዊ ሴራ ተሰርቷል" ብለዋል።

ከዚህ በፊት በአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ በምርጫ ቦርድና በፍርድ ቤት ውሳኔ ተቀባይነት ያለው አመራር ፓርቲውን እየመራ መሆኑን ገልጸው፤ "አንድነት በአንድ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚታወቅ እንጂ የቀድሞውና የአሁኑ የሚባል በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የለውም" ሲሉ አብራርተዋል።

አቶ ትግስቱ አያይዘውም ፓርቲያቸው በአገራዊ ለውጡ በኋላ ወደ አገር ቤት ከገባው ግንቦት ሰባት ጋር ከርዕዮተ ዓለምና ከአስተሳሰበብም ልዩነት ባሻገር፤ ከፓርቲው አመራር አባላት ጋር ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መድረክ ከመተያየት ባለፈ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሰረት በአዋጁ በአንቀጽ 8 እና አንቀጽ 32 ላይ ስለአዲስ ፓርቲ ምስረታ፣ ግንባርና የፓርቲ ውህደት ድንጋጌም የሕግ ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑን አንስተዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያልተመዘገበ ድርጅት ሌሎች ፓርቲዎችን ማፍረስ ካልሆነ በቀር "ህጋዊ ሰውነት የሌለው ድርጅት ውህደት" መፈጸም እንደማይችልም ተናግረዋል።

የግለሰቦችን መደራጀት እንደማይቃወሙ ገልጸው፤ በህጋዊ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤም፣ በማዕከላዊ ኮሚቴውና በአባላቱ ይሁንታ ሳያገኝ እንደተዋሃዱ በፓርቲው ስም መነገዱን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።

አትፓና አንድነት ይህን ይበሉ እንጂ በኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ስለተዋሃዱ ፓርቲዎች ግልጽነት በፓርቲው ምስረታ ወቅት ሁሉም ፓርቲዎች በጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸውን አክስመው መቀላቀላቸውን ለኢዜአ ገልጸው ነበር።

የውህደቱ ስምምነትም ፓርቲዎች በየወረዳው ያሉ አባላትን ዝርዝር በማሳወቅ ከሌሎች ፓርቲ አባላት ጋር በማዋኸድ መስማማታቸውን፤ በሌላ በኩል ከአዲሱ ፓርቲ ምስረታ ጠቅላላ ጉባኤ በፊት የተዋኻዱት ድርጅቶች በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ራሳቸውን ማክሰማቸውን ነበር የተናገሩት።

አትፓ እና አንድነት ፓርቲዎችም ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና በለውጥ ስም የህግ የበላይነት ሲጣስ በቸልተኝነት ከማየት ይልቅ ህግ ማስከበር እንዳለበት ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

ፓርቲዎቹ በስማችን "የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድርገዋል" በሚል የወቀሷቸውን ድርጅትና ግለሰቦች በህግ እንደሚጠይቁም ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸው፤ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ስህተት በፈጸሙ አካላት ላይ ቦርዱ የእርምት እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ ክስ እንደሚመሰርቱ ገልጸዋል።

በአዲሱ ፓርቲ አዲስ ትውልድ ፓርቲን ወክለው ተዋሃዱ ከተባሉት የፓርቲው አባላት መካከል የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ጌታቸው መኩሪያና የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ደነቀን ኢዜአ በስልክ አናግሯቸዋል።

በሁለቱ የፓርቲው አመራሮች እንዳሉትም አትፓ በርዕዮተ ዓለም ከሚመሰሉት ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመጸፈም ደብዳቤ መጻጻፉን፣ በዚህም ስራ አስፈጻሚውና ማዕከላዊ ኮሚቴው ባለፈው መጋቢት ላይ መወሰኑን ገልጸዋል።

ይህን ለማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ቢወሰንም ጉዳዩ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ጊዜ የሚጠይቅና ለወቅታዊ አገሪቱ ሁኔታ በፍጥነት ለመዋሃድ ፈጣን የፖለቲካ ውሳኔ በማስፈለጉ ውህደቱን መፈጸማቸውን አምነዋል።

በሌላ በኩል የስራ አስፈጻሚ የማዕከላዊ ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባኤውን ስራ በወከለው መስራት እንደሚችል በፓርቲው ደንብ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በዚህም ከ9 ስራ አስፈጻሚ አባላት አምስቱ፣ ከ17 የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት 12ቱ በፈረሙበት ሰነድ መሰረት በጋራ ሆነን ሃሳባችን ለመሸጥ "ውህደቱን ፈጽመናል" ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ታፈሰ ሊቀመንበርነታቸው በውክልና እንጂ በምርጫ ቦርድ በኩል የሚታወቀው የፓርቲው ድርጅት ጉዳይ ሃላፊነት እንደሆነ ገልጸው፤ 'ፓርቲው ሲዋሀድ ስልጣኔን አጣለሁ" በሚል ውህደቱን ቢቃወሙም አባላቱ ግን በውህደቱ ተስማምተዋል ነው ያሉት።

ከፓርቲው ቢሮ በህገ ወጥ መልኩ ተስዷል የተባለው ሰነድም የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት የውሎ አበል የተከፈለበት እንጂ ሌላ ሰነድ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በነገው ዕለትም ከፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሰለሞን ታሰፈ ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተው እልባት ለመስጠት ቀጠሮ መያዛቸውንም አክለው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ ኢዜማ ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት አቶ የሺዋስ አሠፋ በስልክ በሰጡን መረጃ፤ አልተዋሃድንም የሚሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ካሉ የራሳቸውን ፓርቲ ውሳኔ ሰጭ አካል መጠየቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"አልተዋሃድን" የሚሉ ፓርቲዎች ከመኖራቸው ባሻገር በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች ውህደት እንዴት ይፈጽማሉ? አዲሱ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ የሚመዘገበው በአዲስ ፓርቲ ወይስ በተዋሃደ ፓርቲ ስም? ስንል አቶ የሺዋስን ጠይቀን ነበር።

በምርጫ ቦርድ ባይመዘገቡም ድርጅቶቹ በህዝብ ልብ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ በምን መልኩ ነው በምርጫ ቦርዱ ፓርቲው የሚመዘገበው ለሚለው ጥያቄ 'ቦርዱ የራሱ አሰራር ይኖረዋል' ሲሉ መልሰዋል። 

የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለምርጫ ቦርድ የጻፉት የትብብር ይደረግልን ጥያቄም ሆነ በቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በተሰጠው የትብብር ይደረግላቸው ምላሽ አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት እንጂ ስለፓርቲዎች ውህደት እንደማያነሳ የኢዜአ ሪፖርተር ታዝቧል።

ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ምርጫ ቦርድን መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ለተለያዩ የቦርድ የስራ ሃላፊዎች በመደወልና በአካል መስሪያ ቤት በመሄድ ጉዳዩን ለማጣራት ጥረት ቢያደረግም ሊሳካለት አልቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም