በኢትዮጵያ የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ሥርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ሊቋቋም ነው

168

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ሥርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አዋጁን ያጸደቀው የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለስልጣኑንለማቋቋም ተብሎ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ የውሳኔ ሀሳብ ከመረመረ በኋላ ነው።

በረቂቅ አዋጁ የዝግጅት ሂደት የተከናወኑ ተግባራት፣ የተለዩ ዋና ዋና ጭብጦች፣ በአስረጂነት በተገኙ የሥራ ኃላፊዎች የተሰጠ ማብራሪያ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች ለምክር ቤቱ አባላት ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ነዳጅ ለሀገር ልማትና ብልፅግና ወሳኝ የኃይል ምንጭ እንደዚሁም  ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶበት ወደሀገር የሚገባ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ምርት ነው።  

አዋጁ ይህንን የምርቱን ባህሪ በማጤን ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ ከማመቻቸት ባሻገር ምርቱ በሰው ጤና፣ በንብረትና በአካባቢ ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ስራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ግብ አለው።  

በዚህም መሰረት አዲስ የሚቋቋመው ባለስልጣን  ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን በማጣራት፣ በማቅረብ፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ፣ በማከፋፈል፣ በመቸርቸር እና ሌሎች ተያያዥነት ባላቸው መስኮች የተሰማሩትን  አካላት ተግባራት ይቆጣጠራል።

ከዚህም ሌላ ባለስልጣኑ የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች ግብይት ተገቢ በሆነ የንግድ አሰራር መመራቱን እና ለህብረተሰቡም በአግባቡ  ተደራሽ መሆኑንም የማረጋገጥ ሥራ ያከናውናል።

የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ የተለያዩ አንቀፆች ላይ ከተከራከሩ በኋላ አዋጁ በአብላጫ ድምጽ፣ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ አዋጅ ቁጥር 1145/2011 በመሆን ፀድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም