የሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ለመላው አፍሪካ ጨዋታ የመሳተፍ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀረ

47

ግንቦት 13/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የመሳተፍ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀረ ። 

የዞን አምስት የመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድር ከትናንት በስቲያ በኡጋንዳ ኢንቴቤ ከተማ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ሩዋንዳ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በማጣሪያ ውድድሩ የሁለተኛ ቀን ውሎ ትናንት ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች መረብ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከኬንያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ በሦስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 0 ተሸንፏል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከትናንት በስቲያ በኡጋንዳ በተመሳሳይ በሦስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 0 የተሸነፈ ሲሆን በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ዞን አምስትን ወክሎ የመሳተፍ ዕድሉ አክትሟል።

ብሔራዊ ቡድኑ  ከመርሃ ግብር ማሟያ ባለፈ ትርጉም የሌለውን የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች መረብ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከአገር ውስጥ ውድድሮች በዘለለ በአህጉራዊና በዞን ውድድሮች ላይ መሳተፍ አለመቻሉ በማጣሪያው ውድድሩ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይሆን አድርጎታል።

በሁለቱ ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስተናገደው የሴቶች መረብ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ወደፊት በተመሳሳይ ጨዋታዎች አሸናፊ እንዲሆን ከወዲሁ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ አመላካች ነው።

ትናንት በተደረገ ሌላ ጨዋታ የኡጋንዳ የሴቶች መረብ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የሩዋንዳ አቻውን በአራት የጨዋታ መደብ 3 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

እስከ አሁን በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ኬንያና ኡጋንዳ  በተመሳሳይ ሁለት ጨዋታዎችን ያሸነፉ ሲሆን ዛሬ ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ እርስ በርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ዞን አምስትን በመወከል ሞሮኮ በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፈውን አገር ይለያል።

 የኬንያ ሴቶች መረብ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ካላቸው ልምድና አቅም አንጻር ኡጋንዳን አሸንፈው በመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ መሳተፋቸውን እንደሚያረጋግጡ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።

የዞን አምስት አባል አገራት የሆኑት ግብጽና ታንዛንያ በመጨረሻው ሰዓት ከማጣሪያው ውድድር ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል።

በመላው አፍሪካ ጨዋታ በሴቶች መረብ ኳስ ውድድር ለመሳተፍ በአፍሪካ በሚገኙ ሰባት ዞኖች የማጣሪያ ውድድሮች ተካሄደው በየዞኑ የአጠቃላይ አሸናፊ የሚሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች በመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም