በትግራይ 177 ወጣቶች ወደ መካከለኛና ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ተሸጋገሩ

64
መቀሌ ግንቦት 29/2010 በትግራይ ክልል 177 ወጣቶችን ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛና ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ተሸጋገሩ፡፡ የክልሉ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ ወደ መካከለኛና ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ለተሸጋገሩ ወጣቶች እውቅና መስጠቱን አስታውቋል። በኤጀንሲው የማኑፋክቸሪንግ አመቻች ዳይሬክተር አቶ ግርማይ ገብረኪዳን ለኢዜአ እንዳሉት ወጣቶቹ የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤት፣ የኮንስትራክሽን ግብአት አቅርቦት ፣ የብረታ ብረት የስራ ዘርፎች ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም ውጤታማ መሆናቸውን በተያዘው በጀት ዓመት በተካሄደው ግምገማ ተረጋግጧል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ ካፒታል ያላቸው ወጣቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ እንዲሸጋገሩ ተደርጓል፤ እውቅናም ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ያፈሩ ወጣቶች ደግሞ ከመካከለኛ ወደ ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሸጋግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአጠቃላይ 174 ወጣቶች ከአነስተኛ ተቋማት ወደ መካከለኛ እና ሶስት ወጣቶች ደግሞ ወደ ትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሸጋግረዋል። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ በክልሉ ከሚገኙ መካከል ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ለማሸጋገር ታቅዷል። 96 ወጣቶች ደግሞ ከመካከለኛ ወደ ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማሸጋገር የመስሪያ ቦታና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ከተሸጋገሩት የመቀሌ ከተማ ወጣቶች መካከል የሁለገብ ብረታ ብረት ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ወጣት በረከት ገብረሚካኤል በሰጠው አስተያየት ከአምስት ዓመት በፊት በሌላ ሰው ድርጅት ተቀጥሮ በወር 5 ሺህ ብር እየተከፈለው ይሰራ እንደነበር አስታውሷል፡፡ የማሽን ፈጠራ ስራ እያሻሸለ እራሱን በመቻል የማምረቻ ድርጅት ከአምስት ዓመታት በፊት በመክፈት አሁን ላይ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳለው ገልጿል። ከራሱ አልፎ አሁን ላይ ከ20 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ያመለከተው ወጣት በረከት "በቀጣይ ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እየሰራሁ ነው" ብሏል። በመቀሌ ከተማ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ መሰሶዎችና ሌሎች የብረታ ብረት ውጤቶችን በማምረት የነበረውን 5ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል ወደ 3 ሚሊዮን ብር መሳደጉን የተናገረው ደግሞ ወጣት ኤፍሬም ሀጎስ ነው። በዚህም ወደ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ መሸጋገሩን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም