የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮፐንሀገኑ አለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ እንዲገኙ ተጋበዙ

68
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዴንማርክ ኮፐንሀገን በሚካሄደው አለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ  እንዲገኙ ተጋበዙ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የስካንዲኔቪያ አገራትን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ ዛሬ ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን በማምራት ከዴንማርክ አቻቸው አንደርሰን ሳሙየልሰን ጋር ተወያይተዋል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን የድንበር ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንድምትፈልግ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በውየይቱ ወቅት ገልጸዋል። ለዓመታት የቆየውን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ችግር በመፍታት ኢትዮጵያ ሙሉ አቅሟንና ሃብቷን ልማት ላይ ማዋል ትፈልጋለች ያሉት ዶክተር ወርቅነህ ይህ እርምጃ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ጠቃሚ ነው ብለዋል። መንግስት እየወሰደ ያለውን የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንቅስቃሴዎችን ለሚኒስትሩ አስረድተዋቸዋል። የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንደርሰን ሳሙየልሰን ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለውን ጠቃሚ እርምጃ አድንቀው መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት በጣም አስፈላጊ ናት፤ ሰላም እንዲመጣ የምታደርገውን ጥረት እናደንቃለን” ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመጭው ጥቅምት ወር ሀገራቸው በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዲገኙ ግብዣ ማቅረባቸውም በመግለጫው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም