አሻራ ማስቀመጥ ሲጀመር ፈታኝ ሲፈጸም አስመስጋኝ መሆኑ ዘላለማዊ እውነት ነው --ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

132

ግንቦት 12/2011  የሸገር ፕሮጀክት ከተማዋን እንደ ስሟ የማስዋብ፣ የማሳመርና ከፍ የማድረግ እርምጃ መነሻ የመደመር ታላቅ ሀሳብና የአርቆ አስተዋይነት ውጤት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትረ ዶክተር አብይ አሕመድ ተናገሩ።

በትናንትናው ዕለት በተካሄደው ‘ገበታ ለሸገር’ የእራት መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ  "በትውልድ ጎዞ ውስጥ አቧራ  ያስነሱም  አሻራ ያተሙም ሰዎች ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የሸገር ፕሮጀክት ከተማዋን እንደ ስሟ የማስዋብ፣ የማሳመርና ከፍ የማድረግ እርምጃ መነሻ የመደመር ታላቅ ሀሳብና የአርቆ አስተዋይነት ውጤት መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‘ገበታ ለሸገር’ ከእራት በላይ የአገር ጉዳይ መሆኑን ነው ያወሱት።

"አቧራ ማስነሳት ቀላል ነው፤ በፍጥነትም በአካበቢው ይዳረሳል፤ አቧራ አይንን ከዕይታ ጉሮሮን አፍኖ ከመናገር ጆሮን ደፍኖ ከመስማት ይከለክላል" ሲሉም ተናግረዋል።

"አሻራ በቶሎም ስም አያስጠራም፤ አድካሚ አሰልቺና ትዕግስትን የሚፈታተን ቢሆንም ሲፈጸም አስመስጋኝ መሆኑ ዘላለማዊ እውነት ነው" ብለዋል።

ዶክተር አብይ እንደገለጹት በታሪክ አጋጣሚ "አሻራ የሚተው ሰዎች አሻራውን የሚተውት ለመንግስት፣ ለፓርቲዎች ወይም ለድርጅቶች አይደለም፤ ለሀገር ሲባል ብቻ ነውም"ለልሲሉ አስረድተዋል።

“ዛሬ የተሰበሰብነው እራት ለመብላት አይደለም፤ አሻራ ለማኖር ነው፤ የከፈላችሁት ገንዘብ ለእራት የሚከፈል አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ስልጣኔ  አሻራችሁን ለማኖር ነው”  ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“ልጆቻችን በዚህ የትውልድ ፕሮጀክት ላይ ስማችሁን ሲያዩት የዛሬው ፎቶግራፋችንን ሲመለከቱት የዚያ ዘመን ትውልድ በወንዞቹ ዳርቻ እየተዝናና በቤተ መጻህፍቱ እያነበበ ይህን አሻራ የተውልንን አባቶቹንና እናቶቹን ሲያመሰግን ምን ሊሰማን እንደሚችል አስቡት” ሲሉም ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ከመስከረም ወፍ እና ከቢራቢሮዎች ከቀዝቃዛ ንፋስ ዝቅ ብለው ከሚበሩ ድንቅ ወፎች ከተኳረፈች መክረሟን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጥፋት ላይ ያለውን የአካባቢ ህይወትና ውበት ፣ እየታየ ያለውን ውድመት እና ጥፋት  "ከመደመር ፍልሰፍና እሳቤ ውጭ መልሶ እንዲያገገም ማስቻል አይቻልም ነው" ያሉት።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ከመባል አልፋ "የአፍሪካ ውብና ጽዱዋ ከተማ የምትባልበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አልማለሁም" ብለዋል።

“እነሆ ከባዱን እርምጃ አንድ ብለን ጀምረናል፤ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ በአረንጓዴ አጸድና በንጹህ ምንጭ መፍለቂያነቷ በአገራችንና በአፍሪካ ተምሳሌት እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደገለጹት መጭው ትውልድ የመስቀል አዕዋፍ ውርውር ሲሉ የአደይ አበባዎች ሲፈኩ ቢራቢሮዎች በየበራቸው ማየት ብርቃቸው አይሆንም።

 “ለዚህ ታላቅ አገር ለዚህች ታላቅ ከተማ ለዚህ ታላቅ ህዝብ ገጽታውን የሚያሳምር፣ ደረጃውን የሚለወጥ አሻራ ለማኖር እንኳን በዚህ ታሪካዊ ስፍራ ተገናኘን፤ እኛ ዛሬ አሻራችንን በክብር እናኖራለን፤ በክብርም በዚህች አገር ታሪክ እንታወሳለን”  ሲሉም ገልጸዋል።

የሸገር ፕሮጀክት ከ200 በላይ ግለሰቦች፣ ዓለም አቀፍና የሀገር  ውስጥ  ድርጅቶች  እንዲሁም ተቋማት በፕሮግራሙ ለመታደም እና አሻራቸውን ለማኖር መቀመጫ ቦታ መግዛታቸው ይታወሳል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ሸገርን ለማስዋብ ፕሮጀክት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ሸገርን የማስዋብ ፕሮጅክት በ29 ቢሊየን ብር  ወጪ  ይፋ የተደረገ ሲሆን በሶስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም