የሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድር በኡጋንዳ አቻው ተሸነፈ

66

ግንቦት 12/2011  በኡጋንዳ እየተካሄደ ባለው የዞን 5 የመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ትናንት የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጎ በኡጋንዳ አቻው ተሸነፈ። 

በኡጋንዳ ኢንቴቤ ከተማ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን ትናንት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ባደረገው ጨዋታ በሦስት የጨዋታ መደብ በኡጋንዳ አቻው 3 ለ 0 ተሸንፏል።

ብሔራዊ ቡድኑ በጨዋታው ጥሩ ፉክክር ቢያደርግም ከደረሰበት ሽንፈት መረዳት እንደሚቻለው ቡድኑ የውድድር ልምድ ማነስ እንዳለበትና ጠንካራ ልምምድ ማድረግ እንዳለበት የሚያመላክት ነው።

የኢትዮጵያ የሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያ አቻቸው ጋር ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ እንደሚያደርግ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

ትናንት በተደረገው ሌላ የማጣሪያ ጨዋታ የኬንያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን የሩዋንዳ አቻቸውን በሦስቱ የጨዋታ መደብ 3 ለ 0  አሸንፏል።

ሩዋንዳ ከኡጋንዳ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው የዛሬ የማጣሪያ ውድድር መርሃ ግብር ነው።

የዞን 5 አባል አገራት የሆኑት ግብጽና ታንዛንያ በማጣሪያ ውድድሩ መጨረሻ ሰዓት ላይ እንደማይሳተፉ መግለጻቸው የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የዞን 5 የመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድር ነገ የሚጠናቀቅ ሲሆን በአጠቃላይ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ በቮሊቦል ውድድር ዞኑን ወክሎ ተሳታፊ ይሆናል።

በአፍሪካ በሚገኙ ሰባት የቮሊቦል ዞኖች ለመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በየዞኖቹ አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆነው ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮው የመላው የአፍሪካ ጨዋታ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም