ባንኩ ለተፈናቃዮች የሶስት ሚሊዮን 900ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ ለተፈናቃዮች የሶስት ሚሊዮን 900ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ዕገዛ የሚውል ሶስት ሚሊዮን 900ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
መቀሌ ግንቦት 12/2011 በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ የንግድ ባንኩ ሰራተኞችም ከደመወዛቸው ቀንሰው 675ሺህ ብር ለተፈናቃዮች እንዲውል ለግሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና ከባንኩ የስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በመሆኑን የገንዘብ ድጋፉን ዛሬ መቀሌ ከተማ ተገኝተው ለክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አስረክበዋል።
አቶ ባጫ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነት ያለው በመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠት ውስኖ እገዛ እያደረገ ነው።
በትግራይ የተደረገው ድጋፍም የዚሁ አካል ነው።
"ለህብረተሰቡ ከሚሰጠው የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው "ብለዋል።
በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከስምንት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት እየገነባ መሆኑን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አስታውቀዋል።
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የገንዘብ ድጋፉን ከተቀበሉ በኋላ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ባንኩ ካደረገው የገንዘብ ድጋፍ በላይ እየተሸረሸረ የመጣው የመከባበርና የመደጋገፍ ባህል ለማደስ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች በክልሉ ተጠልለው እንደሚገኙ ተመልክቷል።