የህዝቦችን የአብሮነት እሴቶች በማጠናከር ድህነትን ለማስወገድ መሥራት ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ

492

ጋምቤላ ግንቦት 12 /2011 በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልሎች ህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነት እሴቶች በማጠናከር ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አመለከቱ። 

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የጋራ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

ርዕሰ መሰተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የጋምቤላና የኦሮሚያ ክልል ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች ናችው ብለዋል።

ስለሆነም በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን  አንደነትና ወንድማማችነት  በማጠናክር  የጋራ ጠላታቸው በሆነው ድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመት እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ አገር የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ የማይፈልጉ ኃይሎች በህዝቦች መካከል መከፋፈልና ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን መመከት የሚቻለው አባቶች ያቆዩአቸውን እሴቶች ሲጎለብቱ መሆኑንም ገልጸዋል።

መድረኩ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነትና አንድነት  ለማጠናከር  የጋራ  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር መዘጋጀቱንም  ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች በደስታም ሆነ በችግር ለዘመናት አብረው መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የህዝቦቹን ወንድማማችነትና የአብሮነት  ለመለያየት  የሚሞክሩ  ኃይሎች  ቢኖሩም፤  ህዝቦቹ ካላቸው የጠነከረ አንድነትና አብሮነት ሙከራቸው አልተሳካላቸውም ብለዋል።  

በተለይም የተለያዩ ኃይሎች በተደራጀ መልኩ መፈናቀልንና መለያየትን ለመፍጠር ቢሰሩም፤ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ያስቀደመው የጋምቤላ ክልል መንግሥት የህዝቦች ሰላም እንዲጠበቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማጠናክር ለህዝቦች ሰላምና የጋራ ተጠቀሚነት መስራት  ይገባልም  ብለዋል አቶ ሽመልስ።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከክልሉ ጋር በልማቱ ዘርፍም አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረክ በሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ዙሪያ ያጠነጠነ  ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።