በሌብነትና በንጥቂያ ወንጀሎች ስጋት ውስጥ ገብተናል....የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች

75

ግንቦት 13/2011  በተደራጀ መልኩ በተሽከርካሪ ታግዞ በሚፈጸሙ የሌብነትና የንጥቂያ ወንጀሎች ምክንያት ስጋት ውስጥ መግባታቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ጥናት ላይ የተመሰረተና ነዋሪዎችን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

አቶ ከበደ ካልሶ በወላይታ ዞን የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ በቅርቡ ከሶዶ ከተማ ለቤት መስሪያ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለመግዛት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጡትን 18 ሺህ ብር ቀን 9:00 ሰዓት ላይ ከባንኩ ደጅ ሳይርቁ በሞተር ሳይክል በመጡ ሰዎች የታገዘ የሌብነት ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል፡፡

“ግለሰቦች አጥንተውና ክትትል አድርገው ወንጀሉን የሚፈጽሙት መሆኑ አሳሳቢ ያድርገዋል” ያሉት ግለሰቡ፣ ይህም በቀጣይ ወጥተው ለመግባት ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቀው እየተከታተሉ ቢሆንም መንግስት ችግሩ እንዲፈታ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

በከተማዋ ዲያስፖራ መንደር የሚኖሩት ወይዘሮ አማረች ዲዳና በበኩላቸው በተደራጀ መልኩ በአደባባይ ጭምር እየተፈጸሙ ያሉ የቅሚያና የሌብነት ወንጀሎች ምክንያት ወጥቶ ለመግባት ስጋት እንደገባቸው ገልጸዋል።

በተለይ አመሻሽ ላይ ለሸመታ ሲወጣ ተንቀሳቃሽ ስልክና ቦርሳ መሰል ንብረቶች ድንገት ሳይታወቅ የሚቀሙና በተደራጀ መልኩ አስፈራርተው የሚወስዱ መኖራቸውን ነው የጠቀሱት። 

ችግሩን ለከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ቢያሳወቁም በቂ የመከላከል ስራ እየተሰራ ባለመሆኑ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

“በወንጀሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ተጠርጣሪዎች በዋስ ስለሚለቀቁ ህብረተሰቡ በፖሊስና በፍርድ ቤቶች አሰራር ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድር አድርጓል” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ 

በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ወንጀል መከልከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን ሞጋ ከነዋሪዎቹ የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰብን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፣ ባለፉት ሁለት ወራት በግልጽና በስውር ወንጀል የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎችን በመለየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በእዚህም በተሽከርካሪዎች ታግዘው የሌብነትና የንጥቂያ ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ከ21 በላይ ግለሰቦች ከሚጠቀሙባቸው 15 ባለሁለት ጎማ የሞተር ሳይክሎችና ሦስት ባለሦስት ጎማ ባጃጅ ታክሲ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን እንዳሉት ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ የመንግስትና የህዝብ ሃብት የሆኑ የውሃና የመብራት መስመሮችን በመቁረጥ በወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው። 

በተደረገው የፍርድ ሂደት በተሽከርካሪ ታግዘው በንጥቂያና በሌብነት ወንጀል ከተጠረጠሩ ውስጥ ሶስቱ ከሦስት ዓመት በላይ እንደተበየነባቸውና ሌሎችም ጉዳያቸውን እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የተለያዩ ተቋማት የአካባቢያቸውን ሠላም ለማረጋገጥ ጥበቃ እንዲያጠናክሩና በከተማዋ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በማስተማር ወንጀልን ከመከላከልና ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ አኳያ ከፖሊስ ጎን እንዲቆሙ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች አየተሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ወንጀለኞች ተመጣጣኝ ብይን ሳያገኙ ይለቀቃሉ የተባለውን ትክክል መሆኑን አምነው ከፍርድ ቤቶች ጋር ባለው አሰራር ቅንጅት እንደሚጎለው ምክትል ኢንስፔክተር ህያውሁን አመልክተዋል፡፡

የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕረሲዳንት አቶ መርዶክዮስ ዴኣ በበኩላቸው “ከፖሊስ ተገቢና አሳማኝ ምክንያቶች ቀርበው ተመጣጣኝ ፍርድ ያልተሰጠበት ወንጀል የለም “ ብለዋል፡፡ 

ነዋሪው ያያቸውና የተፈጠሩ ክፍተቶች ካሉ ህጉ በሚለው መሰረት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም