የሠራዊቱን ስም ለማጉደፍ የሚናፈሱ አሉባልታዎች ሰላምን የማይፈልጉ ኃይሎች ሴራ ነው

101

ግንቦት 12/2011 የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ስም ለማጉደፍ በተለያዩ ቦታዎች የሚናፈሱት አሉባልታዎች ሀገሪቱን ወደችግር ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ኃይሎች ሴራ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተግባሩን ሊታገለው እንደሚገባ ተጠቆመ።

መከላከያ ሠራዊቱ ከሐረሪ ክልል የተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባከናወናቸው ተግባራት በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑም ተመልክቷል።ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ አካላት እንዳሉት ሠራዊቱ እንደትናንቱ ሁሉ አሁንም የአገር አለኝታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል። 

በከተማው ቀበሌ 13 የሚኖሩት መምህር አበበ ወልደሩፋኤል እንዳሉት መከላከያ ሰራዊት ግጭቶች ይከሰቱባቸው በነበሩ የክልሉ አካባቢዎች ላይ በመድረስ የማረጋጋትና ሰላምን የማስፈን ስራ እያከናወነ ይገኛል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ሰራዊቱ ከፌዴራልና ከክልሉ ፖሊስ እንዲሁም ከህብረተሰብ ጋር በመተባበር ያበረከተው አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

መምህር አበበ አንዳሉት የሕይወት መስዋትነት ጭምር በመክፈል የአገር አለኝታነቱን እያረጋገጠ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስሙን ለማጉደፍ መጣር  ተገቢ አይደለም።

የሰራዊቱን ስም ለማጉደፍ የሚሯሯጡት የፖለቲካ አጀንዳ ያልተሳካላቸው አካላት በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጆሮ እንዳይሰጣቸውም አሳስበዋል።

ኢትዮ ጵያ  በዓለም አቀፍ ከምትታወቅበት አንዱ ጠንካራ፣ ሀገር ወዳድ፣ በስነ ምግባር የታነጸና ግዳጁን በአግባቡ የሚወጣ የመከላከያ ሠራዊት በመገንባቷ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዩስፍ ናቸው።

ከሀገር ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ አለኝታነቱን ሲያስመሰክር የቆየና እያስመሰከረ የሚገኝ ሰራዊት መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሠራዊቱ በግለሰብ የሚመራ ሳይሆን ህዝባዊነትን ተላብሶ ለህዝብና ለአገር በመቆም መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ይገኛል።

“ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የሰራዊቱን ስም ለማጉደፍ በተለያዩ ቦታዎች የሚናፈሱት አሉባልታዎች አገሪቱን ወደችግር ለማስገባት የሚጥሩ ኃይሎች ሴራ በመሆኑ ህዝቡ የእነዚህን አካላት ቅስቀሳ ሊቀበል አይገባም” ብለዋል ።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላምመስፈኑን ለአብነት የጠቀሱት አቶ አህመድ ለዚህም መከላከያ ሰራዊት ከጸጥታ አካላትና ከህዝቡ ጋር በጋራ ያከናወነው ተግባር የጎላ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ በቅንጅት የጀመረውን የሰላምና የልማት ሥራዎች በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

“መከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ያሳየ ሠራዊት ነው” ያለው ወጣት አወቀ ወልደገብርኤል በበኩሉ በክልሉ በተግባር ያከናወነው መልካም ስራ ማሳያ እንደሚሆን አመልክቷል።

ህብረ ብሔራዊ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የስም ማጥፋት እንቅሰቃሴ የጀመሩ አካላት  ራሳቸውን  መለስ ብለው እንዲያዩና ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጠቁመዋል።

በምስራቅ ዕዝ ኢንዶክትሬሽን የህዝብ ግንኙነት መኮንን ሌተናል ኮሎኔል አክሊሉ አበበ  በበኩላቸው “የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የአገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ማስከበር እንዲሁም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ በመንግስት የተሰጡት ግዳጆቹ” ናቸው ብለዋል።

እንደ ኮሎኔል አክሊሉ ገለጻ ለውጡን ተከትሎ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲከሰቱ ሰራዊቱ ከክልሉ መስተዳድር በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት ከሌሎች የጸጥታ አካላትና ህዝቦች ጋር በመሆን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እያስከበረ ይገኛል፤ በቀጣይም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።

“ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብራክ የወጣ እንደመሆኑ ሁሉንም ህዝቦች በአንድ ዓይንና በእኩልነት የሚመለከት እና በመርህ የሚመራ ነው” ብለዋል።

ይሁንና ሰራዊቱ እያከናወነ የሚገኘውን መልካም ተግባር ለማጣጣልና ስራውን ለማበላሸት የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ሠራዊቱ በአንዳንድ አካላት እንደሚገለጸው ሳይሆን በህዝቡ ዘንድ የሚወደድና የተከበረ፣ በአገር ውስም ሆነ በውጭ አገር ሰላምን በማረጋገጥ ባከናወነው ስራ ህዝባዊነቱን ያስመሰከረ ሰራዊት መሆኑን አስረድተዋል።

“ሰራዊቱ የሰላምና የጸጥታ ስራውን እያከናወነ የሚገኘው ከህብረተሰቡ እና ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ነው”   ያሉት ሌተናል ኮሎኔል አክሊሉበተለይ ህብረተሰቡ በሰራዊቱ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱ አካላትን ሊቃወማቸውና ፊት ለፊት ሊታገላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እውነተኛ የሰራዊቱን ገጽታ ሊያስተምራቸው እንደሚገባም ነው የገለጹት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም