የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አራት ግብረ ሃይሎች ተቋቁመው ስራ ጀመሩ

60

ግንቦት 13/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎች የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ አራት ግብረ ሃይሎች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።


በተጨማሪም በተወሰኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ያቋረጡ የህክምናና የጤና ባለሙያዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎችና ጥያቄዎቹን አስመልክቶ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በጤናና በህክምና ሳይንስ እጩ ሀኪሞች (ኢንተርን) ተማሪዎች የተነሱት ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው ብሎ ያምናል።

የአዳር ህክምና ሲኖር ያለማቋረጥ ለ36 ሰዓታት በስራ ላይ እንቆያለን፣ ለአዳር ህክምና ያለው የስራ ምቹ ሁኔታ ችግር ያለበት ነው፣ የትምህርት ወጪ መጋራት ስርዓቱም መስተካከል አለበት የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት ነው፣ የምዘና ስርዓቱ ላይ ችግር አለ እና የህክምና ተማሪዎች ሲመረቁ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሰጣል የተባለው የመውጫ ፈተና መቅረት አለበት የሚሉ ጥያቄዎችም በመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪዎች (ኢንተርኖች) የተነሱ ጥያቄዎች መሆናቸውም ተገልጸዋል።

የወጪ መጋራቱን በተመለከተ የመጀመሪያ ዲግሪ የህክምና ተማሪዎች እንደ ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ትክክለኛ ወጪ እንዲጋሩና ከዚህ በፊት ይከፍሉት የነበረው 500 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ሲደረግ የነበረው አሰራራ እንዲቀር በማድረግ ምላሽ መሰጠቱንም አውስተዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

የአዳር ህክምና የስራ ምቹነት ላይ በማረፊያ ቦታና በግብዓት አቅርቦት ላይ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታትም ከዩኒቨርስቲ የስራ ሃላፊዎች ጋር  ውይይት እንደተደረገና እንደ ዩኒቨርስቲዎቹ ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎች የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ ሲባል መሰረታዊ የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ  እጩ ተመራቂ ሀኪም ለመሆን በዩኒቨርስቲዎቹ ከሚሰጠው ምዘና በተጨማሪ አቻ ከሚባሉ ዩኒቨርስቲዎች ያሉ ምሁራን የሚሰጡት ፈተና እንዳለም ጠቅሰዋል።

የነዚህ አቻ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ድርሻ 30 በመቶ እንደሆነና 70 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ራሳቸው የተማሩበት ዩኒቨርስቲው መምህር እንደሆነም አመልክተዋል።

እጩ ተመራቂ ሀኪሞች ከተመረቁ በኋላ የጤና ሚኒስቴር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚሰጥ ገልጸው ከዚያ ውጪ በትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው ዓመት ይሰጣል የተባለው የዩኒቨርስቲዎች መውጫ ፈተና እንደማይሰጥም ተናግረዋል።

 በህክምናና ጤና ሳይንስም ሆነ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች ከዚህ በፊት ምንም አይነት በዩኒቨርስቲዎች የተዘጋጀ የመውጫ ፈተና ተሰጥቶ  እንደማያውቅም ሁሉም አካል ሊያውቀው ይገባል ብለዋል።

በአጠቃላይ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመፍታት የእጩ ተመራቂ ሀኪሞች የስራ ጫና እና መመሪያ፣ የህክምና ጥራት፣ የክፍያ ስርዓትና የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች አስተዳደርን የተመለከተ አራት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ግብረ ሃይሉ የህክምናና የጤና ሳይንስ ትምህርት ቤቶች የስራ ሃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራንንና ባለሙያዎችን ያካተተ እንደሆነና በጥያቄዎቹ ላይ ጥናት አድረገው የመፍትሄ ሰነድ እንደሚያዘጋጁም አመልክተዋል።

ግብረ ሃይሉ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ማድረግ መጀመሩንና የመጀመሪያ ደረጃ የሚባለውን ሰነድ በዚህ ሳምንት ለሚኒስቴሩ አቅርበው ግምግማ እንደሚደረግበትም ነው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ያስረዱት።  

እነዚህ ስራዎች እየተሰሩ ባሉበት ሁኔታ በተወሰኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ጠቅሰዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና  የትምህርት ተቋማቱ ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ የማህበረሰብ ተወካዮች ባሉበት ውይይት በማድረግና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህንንም በመገንዘብ ወደ ትምህረት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎች እስከ ዛሬ ግንቦት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።

በተባለው ጊዜ ውስጥ ተማሪዎቹ የማይመለሱ ከሆነ ህግና ስርዓት ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ የዩኒቨርስቲ ሴኔቶች ባላቸው ህግ፣ደንብና መመሪያ መሰረት እርምጃ እንደሚወስዱም ጠቅሰዋል።

የዩኒቨርስቲ ሴኔቶች ስለሚወስዱት እርምጃ አሁን ላይ ሆኖ መናገር እንደማይቻል የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሴኔቱ አግባብ ነው ያለውን እርምጃ እንደሚወስድም አመልክተዋል።

በአጠቃላይ ሚኒስቴሩ የተነሱ ጥያቄዎችን በዝርዝር አጥንቶ መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋርና ጥያቄውን ካነሱ ተማሪዎች ጋር አሳታፊ በሆነ መልኩ በትብብር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተነሱት ጥያቄዎች እየተፈቱ ያሉና በጊዜ ሂደት በአሰራር ሰርአት የሚፈቱ እንደሆነም ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም