በሩዋንዳ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት በአዲስ አበባ ታሰበ

114

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2019 በሩዋንዳ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት በአዲስ አበባ የእግር ጉዞ በማድረግ ዛሬ ታስቦ ዋለ:: 

የእግር ጉዞው ከአዲስ አበባ ስታዲየም መነሻውን አድርጎ በብሄራዊ ቲያትር - በቤተመንግስት አድርጎ በመስቀል አደባባይ ዞሮ  ፍጻሜውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረገ ነበር።

በዚህ የእግር ጉዞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ፣ በኢትዮጵያ የርዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱሙኩንዴ ጋሳቱራን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት  ተወካዮችና ሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ባደረጉት ንግግር ከ25 ዓመት በፊት በርዋንዳ የዘር መድሎ ችግር በ100 ቀናት ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያለቀበትና አስከፊ ችግር ውስጥ የገቡበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።

ርዋንዳውያን ከዚህ አስከፊ ችግር በመማር ከዘር መድሎና መጠላላት ወጥተው ለኑሮ ምቹ የሆነች አገር መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

ከርዋንዳውያን ትምህርት በመውሰድ ሁሉም በይቅር ባይነት መንፈስ በጋራ ሰርቶ መኖርን ከዚህ ማሳያ ትምህርት መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

አገሮች በተለያየ አጋጣሚ ችግር ውስጥ ቢገቡም ከችግር መውጣት እንደሚችሉ የርዋንዳ ክስተት ማሳያ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንም እርስ በእርስ በመተሳሰብና በጋራ በመስራት አገራቸውን ማሳደግና መለወጥ ላይ እንዲረባረቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የርዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱሙኩንዴ ጋሳቱራ የኢትዮጵያ መንግስት የርዋንዳን የዘር ዕልቂት 25ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ እንዲከበር ላደረገው ድጋፍና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ አገሮች በርዋንዳ አጋጥሞ ከነበረው ቀውስ ትምህርት በመውሰድ በአህጉሩ ሰላም እንዲሰፍን መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እኤአ በ1994 ርዋንዳ ውስጥ ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ በተፈጸመ የዘር ጭፍጨፋ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ህይወታቸውን ማጣቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም