የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት ተካሄዱ

72

ግንቦት 10/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባና በጎንደር ከተሞች ተካሄደዋል
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌዴራል ፖሊስን 29 ለ 22 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉን መሪነት አጠናክሯል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በዘንድሮ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በመሪነት እየገሰገሰ ነው።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 36 ለ 8 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

ጎንደር ላይ መከላከያ ጎንደር ከተማን 23 ለ 21 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ትናንት ዱራሜ ላይ መካሄድ የነበረበት የከምባታ ዱራሜና ቡታጅራ ከተማ ጨዋታ አልተካሄደም። በመሆኑም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በጨዋታው ዙሪያ ውይይት አድርጎ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዛሬ መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ በገንዘብ ችግር ምክንያት ወደ ስፍራው እንደማይሄድ ቀደም ብሎ ማሳወቁን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ደንብ መሰረት ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታውን እንደማያካሄድ ቀድሞ በማሳወቁ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በፎርፌ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 ውጤት እንዲያገኝ ተደርጓል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ24 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ21 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ18 ነጠብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ጎንደር ከተማ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን አስረኛ ደረጃን ይዟል።

በሌላ በኩል በሐበሻ ሲሚንቶ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል።

ሶዶ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን በሶስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 0፤ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ ሙገር ሲሚንቶን በአምስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ተስተካካይ ጨዋታው የስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሲሆኑ ወላይታ ድቻ እና ሙገር ሲሚንቶ በወቅቱ በግብጽ በተካሄደው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ሻምፒዮና ተሳታፊ በመሆናቸው የተራዘመ ነበር።

በስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በጣና ባህርዳር የፋይናንስ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተራዝሞ ዛሬ መካሄድ የነበረበት የጣና ባህርዳርና የመከላከያ ተስተካካይ ጨዋታ መከላከያ በተጫዋቾች ጉዳትና በዝግጅት ማነስ ምክንያት ጨዋታው ይራዘምልኝ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት በማግኘቱ ጨዋታው ለሌላ ጊዜ መዘዋወሩ የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ31 ነጥብ ሲመራ፣ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ26 ሙገር ሲሚንቶ በ20 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም