የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን አጸዱ

133

ግንቦት 11/2011 ሁለተኛውን አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ምከንያት በማድረግ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን አጸዱ።

ነዋሪዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠራውን የጽዳት ዘመቻ መሠረት በማድረግ ዛሬ ማለዳ ከ12፡00 ጀምሮ በከተማው ዋና ዋና መንገዶች በመዘዋወር አካባቢያቸውን አጽድተዋል፡፡

“አካባቢያችንን ከቆሻሻ ውስጣችንን ከቂምና ከጥላቻ እናጽዳ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በተካሄደ ሀገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻነዋሪዎቹ  የተደፈኑ የፍሳሽ ቆሻሻ መውረጃዎችን በመክፈት የጽዳት ሥራውን አከናውነዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጽዳቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታደሠ ደጀን የሚኖሩበትን አካባቢና ከተማን ማጽዳት ጠቀሜታው ለራስ መሆኑን ተናግረዋል።

የጽዳት ሥራ የነዋሪው የውዴታ ግዴታ መሆኑን ጠቁመው ከዘመቻ ሥራ በተጨማሪ ሁሌም አካባቢን ማጽዳት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። 

ጽዳት ከራስና ከቤት እንደሚጀምር የሚገልጹት አቶ ታደሰ “ሁሉም ቆሻሻን በአግባቡ ቢያስወግድና አካባቢውን ቢያጸዳ አገር ትጸዳለች” ብለዋል፡፡

እንደአስተያየት ሰጪው ገለጻ ኃላፊነት የማይሠማቸው ጥቂት ግለሰቦች በየቦታው የሚጥሉት ቆሻሻ በተለይ በክረምት ወቅት ፍሳሽ መውረጃ ትቦዎች ተደፍነው የከተማው መንገድ ለብልሽት እየዳረገ ይገኛል።

ሕብረተሰቡ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት ህዝቡን አስተባብሮ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል፡፡

 “ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻን ዕለታዊ ማድረግ ከተቻለ ከተማችንን በዘላቂነት ማጽዳትና ማስዋብ እንችላለን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አሥራት እጀታ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።

“ዘረኝነት እና ቆሻሻ ህብረተሰብን ጎጂ በመሆናቸው ይመሳሰላሉ” ያሉት አስተያየት ሰጪው ሁለቱንም ፈጥኖ ማስወገድ ካልተቻለ ጉዳታቸው የከፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ዛሬ ማለደ በአሶሳ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ የጽዳት መሳሪያዎችን ይዘው አካባቢያቸውን ሲያጸዱ መስተዋላቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።