10ኛው የመላው አፍሪካ ቆዳ ንግድ ትርኢት የፊታችን አርብ በአዲስ አበባ ይከፈታል

85
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 ከ100 በላይ የውጭና ሀገር ውስጥ ደርጅቶች የሚሳተፉበት 10ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርዒት የፊታችን አርብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም  አዳራሽ ይከፈታል። የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ከቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የንግድ ትርዒት ከመጭው ዓርብ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከአንድ ሺህ የሚልቁ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ታጠቅ ይርጋ ዝግጅቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ  በትርዒቱ ላይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ኢንስቲትዩቶችን ጨምሮ ከ100 በላይ ድርጅቶች በመሳተፍ ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ። የአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ጨምሮ ከ25 ሀገሮች በላይ የዝግጅቱ ታዳሚዎች ይሆናሉም ብለዋል። ከንግድ ትርዒቱ በተጓዳኝ በገዥወችና ሻጮች መካከል የኢንቨስትመንት ጉባኤዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የደረሰችበትን  ደረጃ የሚያሳይ የፋሺን ትርዒት እንደሚቀርብ አቶ ታጠቅ ገልፀዋል። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የንግድ ትርዒቱ  በምርት አቅራቢዎችና ገዥዎች መካከል የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የውጭ ንግድን ለማበረታታት እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ሚና ይጫወታል። በአዲስ አበባ ለአስረኛ ጊዜ የሚካሄደው ትርዒቶች ሀገሪቷ በመስኩ ያላትን አቅም በማስተዋወቅ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተፈላጊነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አቶ ታጠቅ ጠቅሰዋል። ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ማህበሩ 11ኛውን የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርኢት መቀመጫው ጀርመን ከሆነውና መሰል ሁነቶችን በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ ልምድ ካለው ˝ቲ ኤፍ ሲ መሴ ፍራንክ ፈርት˝ ከተሰለው ተቋም ጋር በትብብር ማዘጋጀት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል። የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ በመላው ዓለም ከ150 ሀገራት ጋር ትስስር ያለው በመሆኑ ትልልቅ ገዥዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ የገበያ አድማሱን ለማስፋፋት አወንታዊ ሚና ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም