ሠራዊቱ በግጭት ወደሱዳን ተሰደው የነበሩ 1ሺ 500 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መልሷል

105

ግንቦት 11/2011 በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወደጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደው የነበሩ 1ሺ 500 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ33ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ተናገሩ፡፡

በግጭቱ ከጎንደር ሱዳን ተስተጓጉሎ የነበረው የነዳጅ ቦቴዎች ትራንስፖርትና የወጪ ንግድ ወደ ቀደሞ እንቅስቃሴ መመለስ መቻሉ ተገልጿል፡፡

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አለሙ አየለለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት ወራት የተመለሱት ዜጎች ከመተማ አካባቢ ግጭቱን ሸሽተው በሱዳን ገለባትና ገዳሪፍ ተሰደው በመጠለያ ውስጥ የቆዩ ናቸው፡፡

በሁለቱ ሀገሮች ድንበር አካባቢ በሚገኙ የመከላከያ አዛዦች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት እንዲመለሱ የተደረጉት ዜጎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ መጀመራቸውን አዛዡ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ስጋት አድሮባቸው ያልተመለሱ 200 ዜጎችን በቅርቡ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ አዛዦች የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ብርጋዴር ጀነራል አለሙ እንዳሉት ሠራዊቱ በተሰጠው የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ተልእኮም በግጭቱ ምክንያት ከጎንደር መተማና ሱዳን ተቋርጦ የቆየውን የትራንስፖርት ስምሪትና የወጪ ንግድ ወደነበረበት መመለስ ተችሏል።

“በአሁኑ ወቅት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ያለአንዳች የጸጥታ ስጋት በየእለቱ ነዳጅ በማጓጓዝ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

በአካባቢው በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ላኪዎችና አስመጪዎች በሱዳን በኩል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከመግባቱ በፊት የጎንደር መተማና ሁመራ መንገዶች የትራንስፖርት ስምሪት በወታደር ታጅቦ ይካሄድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“በአሁኑ ወቅት ይህ ሁኔታ በመቀየሩ አሽከርካሪዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ስምሪት እያደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡

ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ሽፋን በማድረግ አሽከርካሪዎችን አፍኖ በመውሰድ በገንዘብ ተደራድሮ የመመለስ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ህገ-ወጥ ግለሰቦችን ሠራዊቱ ተከታትሎ ለህግ በማቅረቡ ስጋቱን መቀነስ እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩና ባለሀብቱ በመጪው የክረምት ወራት ያለምንም የጸጥታ ስጋት ወደ እርሻ ስራቸው እንዲገባ ለማድረግም ሠራዊቱ ከአካባቢው መስተዳድሮች ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን የጸጥታ ሥራ ለመስራት ዝግጅት መደረጉንም አዛዡ አያይዘው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም