የአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር እድገት ከከተማዋ እድገት ጋር አለመጣጣሙ የአኗኗር መዛባትና የገጽታ መበላሸትን አስከትሏል - ምሁራን

161

ግንቦት 10/2011 የአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር እድገት ከከተማዋ እድገት ጋር አለመጣጣሙ የአኗኗር መዛባትና የከተማዋ ገጽታ መበላሸትን  እንዳስከተለ  በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋየ ተሾመ ገልጸዋል።

ከተማዋ ስትመሰረት ደን፣ ወንዝ፣ የዱር አራዊት እና አዕዋፋት በአካባቢዋ በስፋት እንደነበሩ የገለጹት ምሁሩ፤ በሂደት የህዝብ ቁጥሩ በመጨመሩ ተፈጥሯዊ ሃብቶች መውደማቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋየ አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ የአየር ሁኔታ በሰው ሰራሽ ምክንያቶች እንደተለወጠና ወንዞቿ ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆነ የቆሻሻ ማስወገጃ መሆናቸውን  የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ እነዚህ ሁኔታዎች የተከሰቱት የተቀናጀ  የከተማ ማስተር ፕላንን ባለመተግበሯ  ነው ይላሉ።

በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህርና አርክቴክት ሙሉጌታ በቀለ በበኩላቸው፤ ከከተማዋ የህዝብ ቁጥር አኳያ በቂ መሰረተ ልማት፣ በቂ የህዝብ አረጓዴ ስፍራዎች፣ የመኖሪያ ቤት እንደሌለ ገልጸው ይህም ውስን ሀብትን በትክክል ካለመጠቀም የመነጨ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ወንዞችን ጨምሮ ብዙ የተፈጥሮ ስጦታዎች የታደለች ቢሆንም በእቅድ ካለመመራትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር የተነሳ ጉዳታቸው ማመዘኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ወንዞች የፋብሪካዎች ተረፈ ምርት እና ከየመኖሪያ ቤቱ የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻ የሚለቀቅባቸው በመሆኑ ህብረተሰባዊ ጠንቅ ሆነዋል ነው ያሉት።

ከተሜነት የእድገት ምልክት ቢሆንም ተፈጥሮን እየበከለ ከሆነ ግን ጉዳቱ እንደሚያመዝን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር፤ አዲስ አበባ በሀሩር አውራጃ  ብትገኝም ሙቀትና ጨረር የሚጨምሩ መስታወታማ ህንጻዎች መበራከታቸውን አስደንጋጭ ብለውታል።

ከተማዋ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ መሆኗ ቢያስደስትም፤ በዓለም ላይ ሶስተኛዋ ግዙፍ ከተማነቷን እንዳታስጠብቅ የሚያደርጉ የደቀቁ ሰፈሮች ባበሌት መሆኗንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ መሪዎች በአንድ ወቅት አዲስ አበባን ለመሰብሰቢያነት ተጠይፈዋት እንደነበር ያነሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ለውጦች እየታዩ እንደሆነ ገልጸዋል።

በከተማ የልማት እቅድ የመሬት አጠቃቀም ወሳኝ ነው ያሉት አርክቴክቱ፤ የንግድ፣ የመኖሪያ፣ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ መሰረተ ልማት በእቅዱ መሰረት መተግበር ቢኖርበትም አዲስ አበባ አዲስ አበባ ብዙ ነገር ይጎድላታል ነው ያሉት።

የኢንዱስትሪ አካባቢዎችን፣ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን፣ የአገልግሎት ተቋማትንና  መኖሪያ ቤቶችን በተገቢ የመሬት አጠቃቀም መተግበር እንደሚገባ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋየ ገልጸዋል።

አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የተነደፈው“ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” እቅድ የከተማዋን መጥፎ ገጽታ እንደሚቀይር ተናግረዋል።

እቅዱ የመሃል ከተማዋ አካባቢ አረንጓዴ ቦታ እንዲሆንና ለህዝብ ሁለገብ መዝናኛ አገልግሎት መታቀዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።

አርክቴክት ሙሉጌታ  በበኩላቸው መንግስት ወንዞችን ለማጽዳት የጀመረው እንቅስቃሴ እንደሚሳካ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮን በመጥቀስ  አብራርተዋል።

የለንደኑ ቴምስ ወንዝ በተለያዩ ቆሻሻዎች ማፋሰሻነት ምክንያት የተበከለ ወንዝ እንደነበር አንስተው፤ አሁን በዓለም በጎብኝዎች ተመራጭና ንጹህ ወንዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን ወደ ተፈጥሯዊ ሀብቷ እንደሚመልስ ና  በአካባቢው ለሚሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገልጸዋል።

ፓርኮንች የማልማትና ወንዞችን የማጽዳት እቅዱ ላይ ነዋሪውም በመሳተፍ የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት በተግባር ማሳየት እንደሚገባ መክረዋል።

አካባቢው አረንጓዴና ንጹህ አየር ያለው ሲሆን ማህበራዊ እርካታን እንደሚፈጥር የጠቀሱት አርክቴክት ሙሉጌታ፤ ንጹህ አየርና አካባቢ ስለሚፈጥርም ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም