ተገቢ ጥያቄዎች ለምናከሄደው ሪፎርም አቅም የሚፈጥሩ ናቸው – ዶክተር አሚር አማን

149

ግንቦት 10/2011 የጤና ባለሙያዎች ለማህበረሰቡ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ፍላጎት የመነጨ የሚያነሱት ጥያቄ በጤና ዘርፍ ለተጀመረው ሪፎርም አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ገለጹ።

የጤና ባለሙያዎች ለማህበረሰቡ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ፍላጎት የመነጨ የሚያነሱት ጥያቄ በጤና ዘርፍ ሪፎርም አቅም እንደሚፈጥር የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ገለጹ።


የኦሮሚያ ክልል የጤና ባለሙያዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ በማተኮር የተካሄደው የሁለት ቀናት ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።

የኦሮሚያ ጤና ባለሙያዎች በውይይቱ ወቅት ላነሱዋቸው ጥያቄዎች የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ምላሽ ሰጥተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በውይይቱ ወቅት የክልሉን የጤና ዘርፍ ተግባራትን በመዳሰስ የጤና ባለሙያዎች ያቀረቡዋቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል።


ዶክተር ደረጀ፤ የጤና ባለሙያዎቹ ከወጪ መጋራትና ትምህርት እድል፣ ከስራ ፈቃድ፣ ከጤና ተቋማት አገልግሎት ጥራትና አቅርቦት፣ ከመኖሪያ ቤትና የሙያ መድህን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚን በሰጡት ማብራሪያ፤ የጤና ባለሙያዎቹ ባነሱዋቸው ጥያቄዎች ተገቢነት ላይ መንግስት እምነት አለው። ያለባለሙያዎቹ ተሳትፎም ስራውን ለማከናወንና ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ነው ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ለማህበረሰቡ የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ከመስጠት ፍላጎት የመነጨ መሆኑንም ጠቁመው፤ ይህንን በተገቢው መንገድ ለበጎ ከዋለ እየሰራን ላለው የዘርፉ ሪፎርም ትልቅ ግብዓት ሊሆን እንደሚችል አጽንኦት ሰጥተውታል።

ዶክተር አሚር እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም የሚስተዋለው የተቆራረጠ የመድሃኒትና ህክምና መሳሪዎች ግዥም በተሻለ መንገድ ለማከናወን ታቅዷል። 


ይህም በዓለም ከታወቁ ኩባንያዎች ጋር በሚገባ የሶስት ዓመት ማዕቀፍ ግዥ አሰራር እንደሚተካም ነው ያመለከቱት።

የጤና መድህን ጉዳይ በፌዴራል መንግስት ተወስኖ ተግባራዊ እንደሚሆን ያመለከቱት ዶክተር አሚር፤ በክለሳ ላይ ያለው የጤና ፓሊሲው ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ የራሳቸውን ግብዓት እንዲያክልበት በተቋሙ ድረ ገጽ መለቀቁን አውስተዋል።


የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት ባለሙያዎቹ ያነሱት ጥያቄዎችን ተገቢነት ያምንበታል። መንግስትም ለህዝብ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ግብ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት፤ የፌዴራሉ የጤና መድህን ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች በሚሰሩበት ሆስፒታል የነጻ ህክምና እንዲያገኙ፣ በያሉበት በማህበር በመደራጀት ህጉ የሚጠይቀውን መስፈርት ካሙዋሉ መንግስት የመኖሪያ ቦታ እንዲሰጥ ወስኗል።

በኦሮሚያ ክልል 1 ሺህ 400 ጤና ጣቢያዎች፣ 81 ሆስፒታሎች፣ ሰባት ሺህ የጤና ኬላዎች እንደሚገኙና በጤና ተቋማቱም ከ72 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያሳያል።