ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ ቢሆንም ስራ ማቆምና ሰላማዊ ሰልፉን ሙያችሁ አይፈቅድም – ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

205

ግንቦት 10/2011 በጤና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም ስራ ማቆምና ሰላማዊ ሰልፉ ከሙያው ስነ ምግባር አኳያ ተገቢ አለመሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የኦሮሚያ ክልል የጤና ባለሙያዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ያተኮረውና ትናንት የተጀመረው ውይይት ዛሬ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማንና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ባሉበት ውይይት ተካሄዶበታል። 

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከወጪ መጋራት፣ ከትምህርት እድል፣ ከሙያ ስራ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ከጤና ተቋማት አጠልግሎት አሰጣጥ ጥራትና አቅርቦት፣ ከመኖሪያ ቤት፣ ከሙያ መድህንና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። 

የክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ከመስጠትና የተሻለች አገር ከመፍጠር ከተቆርቋሪነት የተነሱ ናቸው። 

የክልሉ መንግስት የእለተ ተእለት አገልግሎታቸውን ሳያጓድሉና ስራን ሳይበድሉ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ጥያቄያቸውን ላቀረቡት የጤና ባለሙያዎች ትልቅ ክብር እንዳለው ያወሱት አቶ ሽመልስ፤ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት የክልሉ መንግስት የጤናውን ዘርፍ ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት  መንግስት ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ “በየትኛው ዘርፍ ለአመጽ የትኛው ጉዳይ  እንደሚጋብዝ አጥንተውና በጀት መድበው የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳያደርጓችሁ” ብለዋል። 

አገሪቷ ካለችበት ወቅት አኳያ “ጥያቄዎቻችሁንና አካሄዳችሁ የተጠና መሆን ይገባዋል” ሲሉ አሳስበዋል። 

የእንደምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ የጤና ባለሙያው ጥያቄና በማህበራዊ ሚዲያው የሚናፈሰው ወሬ ለየቅል ነው። አሁን የተነሳው ጥያቄ በአገሪቷ ውስጥ በሁሉም ዘርፍ፣ በሁሉም ቦታ ያለ ነው። ዛሬም “አገልግሎት አጥቶ በየቦታው የሚሞቱ ህብረተሰብ ክፍሎች ያለን መሆኑ መረሳት የለበትም” ብለዋል።  

ይህን ዓይነቱን ህዝብ ከችግር ማውጫው ግን በራስ መስዋዕት መሆንንም ይጨምራል፤ አድማና ስራ ማቆሙን ግን ሙያችሁም፣ ወቅቱም አይፈቅድም፤ የሌላ አካል መጠቀሚያ እንዳይሆንም መጠንቀቅ አለብን ብለዋል።

የዘርፉ ችግር ውስብስብ ቢመስልም የባለሙያው ተነሳሽነትና የሙያ ስነ ምግባር እንዲሁም የመንግስት ቁርጠኛነት ከታከለበት የሚፈታ መሆኑን አጽንኦት ሰጠውታል። 

የዛሬው ትውልድ ይህን ህዝብና አገር የማሻገር አደራ እንደተሰጠው የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ አሁን መሆን የሚገባው ጥያቄም ይህን ህዝብና አገር በየትኛው አቅጣጫ እንቀይር  መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። 

በአገሪቷ በፖለቲካው ዘርፍ የተገኘውን ድል ወደ ኢኮኖሚው በማዞር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።