የአሜሪካው ‘አትሌት ኢን አክሽን’ የቅርጫት ኳስ አካዳሚ የፊታችን አርብ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር ይጫወታል

124
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 የአሜሪካው ‘አትሌት ኢን አክሽን’ የቅርጫት ኳስ አካዳሚ የፊታችን አርብ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ቡድን ጋር ይጫወታል። አካዳሚው ከአራት ቀናት በፊት አንስቶ በኢትዮጵያ የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብሩን እያካሄደ ሲሆን እስካሁን በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲና ከኢትዮጰያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጓል። የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብሩን ያዘጋጁት የቅርጫት ኳስ አካዳሚው ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና ከአዲስ አበባ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነው። በዚሁ መሰረት የአካዳሚው የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲን 65 ለ 21 የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚን 61 ለ 21 በሆነ ውጤት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ሃይሌ ለኢዜአ ገልጸዋል። አካዳሚው ከነ በስቲያ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም ከቢጂአይ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ወልቂጤ ላይ ከወልቂጤ ከተማ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ከወዳጅነት ጨዋታው በተጨማሪ በአዲስ አበባ በሚገኙት የጎሮ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የቤተል መካነየሱስ ትምህርት ቤት እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ ለሚገኙ የታዳጊ ወጣቶች የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች አጭር ስልጠና እንደሚሰጥም አክለዋል። የአካዳሚው ተጫዋቾችና አሰልጣኞች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የወዳጅነት ጨዋታና የስልጠና መርሃ ግብሩን አጠናቀው ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል። እንደዚህ አይነት የስልጠናና የወዳጅነት ጨዋታዎች መኖራቸው በቅርጫት ኳስ ስፖርት የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገራት ልምድ ለመቅሰምና ያሉ ክፍተቶችን በመመልከት የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝም ነው አቶ ይመር ያስረዱት። በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተተኪዎችን ለማፍራት እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የተሻለ ተሞክሮ እንዲያገኝ  ከቅርጫት ኳስ አካዳሚ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም በድጋሚ ይጫወታል ብለዋል። መረጃዎች  እንደሚያመላክቱት  የኢትዮጵያና ቅርጫት ኳስ ትውውቅ 1930ዎቹ ላይ ይጀምራል። ዳግማዊ ሚኒሊክ፤ ተፈሪ መኮንን፤ ኮከበ ፅባህና ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ስፖርቱ በኢትዮጵያ አሀዱ ያለባቸው ናቸው። ቅርጫት ኳስ በአገራችን አንጋፋ ከመሆኑ ባሻገር በ1970ዎቹ እጅግ ተወዳጅና በተለይም በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘና ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ቢሆንም  ከጊዜ በኋላ ግን እየተዳከመ  መጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም