የቱሪዝም ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች እየተዘረጉ ነው

209

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2011  በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንደስትሪው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በማቃለል የዘርፉን ልማት ማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የቱሪዝም አድገቷ 48 ነጥብ 6 ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው አማካይ 3 ነጥብ 9 በመቶ እና የአፍሪካ አማካይ የ5 ነጥብ 6 በመቶ የዘርፉ እድገት በእጅጉ የላቀ ውጤት ነበር ተብሏል።

ይሁንና አሁንም በዘርፉ ውጤታማ የንግድ ሥርዓት አለመኖር፣ የፋይናንስ ውስንነት፣ አስፈላጊ የመሰረተ-ልማት አለመሟላት ችግሮች ይስተዋላሉ።

በባህልና ቱሪዝም የቱሪዝም አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ደርበውም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታትም በፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የማሻሻያ ተግባራት ተከናውነዋል።

ጎን ለጎንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተሰራው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተጓዳኝም ሁለት የነበረውን የሥራ ክፍል ወደአራት የሥራ ክፍል እንዲበተን በማድረግ በሚኒስቴሩ ያለውን የሥራ ጫና ማቅለል ተችሏል ብለዋል።

በዚህም አሁን ላይ የንግድና የማስተዋወቅ አንዲሁመ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥራዎች በተናጠል አንደሚሰሩ ነው ያብራሩት። 

የአገሪቱ ሎጆች፣ አስጎብኚዎችና የሆቴል ኢንደስትሪዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ የማሻሻል ሥራም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአገር ውስጥ የቱሪዝም ሰትራቴጂ ከዚህ ቀደም አንደሌለና አሁን ላይ ግን ተዘጋጅቶ በባለድርሻ አካላት ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው የአገሪቱን ቱርዝም ኃብት በቅጡ ያለማስተዋወቅ ችግር ይታያል።

ለዚህም ደግሞ የማስተዋወቂያና የዘርፉ ንግድ ስትራቴጂ በአግባቡ አለመተግበሩን ነው ለአብነት ያነሱት።  

ያም ሆኖ ዘርፉን ለማስተዋወቅና ባህላዊና ዘመናዊ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

በተለይም የቱሪዝም ፍሰቱን በቅጡ ለማጤን የሚያስችል የቱሪዝም የመረጃ ቋትና ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ ያለውን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምንም እንኳን የቁርጠኝነትና የመቀናጀት ክፍተት ቢኖርም ድርጅታቸው ችግሩን ለማቃለል ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዘርፉ ትክክለኛ መረጃ የሚያቀርበው ይኸው የመረጃ ሥርዓት ረጅም ጊዜ መረጃዎችን ለመሰብሰበ ይወስድበታል ተብሏል።