በድሬዳዋና አካባቢዋ ዛሬ የአቧራ ማዕበል ተከስቷል

79

ግንቦት 10/2011 በድሬዳዋና አካባቢዋ የተከሰተው የአቧራ ማዕበል ዝቅተኛ የአየር ግፊት ወደ ሰሜን ንፍቀ ክበብ በሚጓዝበት ወቅት የሚከሰት መሆኑን አንድ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ምሁር ገለጹ።
በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዮናስ ታደሰ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ክስተቱ ዝቅተኛ የአየር ግፊት ወደ ሰሜን ንፍቀ ክበብ በሚጓዝበት ወቅት የሚፈጠር ነው። 

"ከየመን ዝቅተኛ ስፍራ ተነስቶ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድን እንዲሁም ድሬዳዋና አካባቢውን ያዳረሰውም ክስተት አቧራማና እርጥበት የቀላቀለበት ንፋስ የፈጠረው ነው" ብለዋል። 

ከተማዋን ለአንድ ሰዓት ያዳረሰው ይህ ንፋስ ዕፀዋት በሌለበት ስፍራ በፍጥነት ስለሚጓዝ ማንኛውንም ነገር ሊያስወግድ እንደሚችል ገልጸዋል።

ነገር ግን የምስራቅ የአገሪቱ ሰንሰለታማ ተራራዎች በዕፀዋት መሸፈናቸው የንፋሱ ፍጥነትና ጥፋት ሊያስቆሙት እንደሚችሉም አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን  የሰጡ የድሬዳዋ  ከተማ ነዋሪዎች ክሰተቱን ከመገረምና ከመንፈሳዊ ሁኔታዎች ጋር አያይዘውታል።

ከጠዋቱ 4 ሰዓት ተኩል ጀምሮ እስከ 5 ሰዓት ከ40 ድረስ ንፋስ የቀላቀለ አቧራ ከተማዋንና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በመጋረድ ጨለማ ፈጥሯል።

ተሽከርካሪዎች ክስተቱን ተከትሎ መብራት በመጠቀም ተገልግለዋል።የተሰጡ ልብሶች በአቧራው ተበላሽተዋል። ለሽያጭ የቀረቡ የምግብ ሸቀጦች በአቧራው መበላሸታቸውንም የኢዜአ ሪፖርተር ተመልክቷል።

የባለ ሶስት እግር የታክሲ አሽከርካሪ ወጣት ሰይፉ ገብረ ማርያም በሰጠው አስተያየት ''ክስተቱ ያስፈራል፣ በጉዞ ላይ ሳለሁ ድንገት መከሰቱ አስፈርቶኝ ነበር፣ ግን እየቆየ ድንጋጤው ሲለቅኝ ፈጣሪዬ ከክፉ ነገር ጠብቀኝ ብዬ ፀልያለሁ'' ብሏል።

ወይዘሮ ዘሃራ መሐመድ በቀን ሲጨልም በማየታቸው ድንጋጤ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።በወቅቱ የተሰማቸውን ፍርሃት በማሰብ በዕምነታቸው ክፉ ነገር እንዳይገጥማቸው ፈጣሪያቸውን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

የሳቢያን ነዋሪ አቶ ንጉሴ አየለ በከተማዋ ተመሳሳይ ክስተት ከአራት ዓመታት በፊት ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፣ የአሁኑ ክስተት እንዳላስደናገጣቸው ተናግረዋል።

ተማሪ የኋና ሀብታሙ ክስተቱ በተፈጠረበት ወቅት የማካከሻ ትምህርት እየተማሩ እንደነበር ትናገራለች።

''እኔ እጅግ ደንግጬ ሰውነቴ ሁሉ ደነዘዘ፣ አስምና የመተንፈሻ አካል ችግር የነበረባቸው ልጆች ግን አቅቷቸው ተዝለፍልፈው ወድቀዋል'' ስትልም ተናግራለች።

የመልካ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱላሂ እድሪስ በበኩላቸው አቧራ እንደ ጎርፍ ሲጓዝ ባዩ ጊዜ መደንገጣቸውንና መገረማቸውን ይናገራሉ።

በተመሳሳይ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በቁልቢ ከተማ በታየው ተመሳሳይ ክስተት ግርምት እንደፈጠረባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በከተማው 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ህሩይ ወልደ ሥላሴ በስልክ እንደተናገሩት ድርጊቱ ''አዲስና ለማመን  አስቸጋሪ''ሲሉ ይገልጹታል።

''በጣም በመጨለሙም ግርምት፣ፍርሃትና መደናገጥን ፈጥሮብኛል፤ ለየት ያለ ነገር ነው ያየሁት''ብለዋል።

ተመሳሳይ ድርጊት ከሰድስት ዓመታት በፊት መመልከታቸውን የተናገሩት መምህር ውብሸት ዓለማየሁ፣ ''የዛሬው ጨለማና አስፈሪ፣ ተሽከርካሪዎችም መብራት ሲያበሩ ነበር'' ሲሉ እማኝነታቸውን ገልጸዋል።

ክስተቱ ለአሥር ደቂቃ መቆየቱን ያዩት እማኝ፣ ክስተቱ ሲያበቃ ከተማዋ ወደ ብርሃኗ በመመለሷ ሕዝቡም ተረጋግቷል  ብለዋል።

ቁልቢ ከሐረር 70 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ከተማ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም