የዝዋይ ሀይቅ ጥልቀቱ በሶስት እጥፍ ምርታማነቱ ደግሞ በአራት እጥፍ ቀንሷል

306

ግንቦት 10/2011 የዝዋይ ሐይቅ የውሃው ጥልቀት በሶስት እጥፍ የሚሰጠው የዓሳ ምርት መጠን ደግሞ በአራት እጥፍ መቀነሱ ተገለፀ ።

ሐይቁ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በእምቦጭ አረም እየተጠቃና ለጥፋት እየተጋለጠ መምጣቱን በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል መረጃ ይጠቁማል ።

በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማእከል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ለማ አበራ ለኢዜአ እንደገለፁት ከዝዋይ ሀይቅ ከአራት ዓመታት በፊት በዓመት በአማካይ ከ4ሺህ 500 እስከ 6ሺህ ቶን ዓሳ ይመረት ነበር ።  

“አሁን ግን የሐይቁ የዓሳ ምርት ከ1ሺህ ቶን ያነሰ ነው”ብለዋል ።

የሐይቁ ውሃ ጥልቀቱም ቢሆን ከ12 ሜትር ወደ 4 ሜትርና ከዚያ በታች መውረዱን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።

“ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በሐይቁ የእምቦጭ አረም እየተስፋፋ ነው” ያሉት የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ይህም ሐይቁ እየተበከለ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል ።

የዝዋይ ሐይቅ ብቻ ሳይሆን በስምጥ ሸሎቆ የሚገኙ ሌሎች ሃይቆችና የውሃ አማራጮች እየተጎሳቆሉና እየደረቁ መሆናቸውን ጠቅሰው አካባቢው ለእሳተ ጎሞራ እንዳይጋለጥ ሃይቆቹን መጠበቅ የውዴታ ግዴታ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል ።

“ምክንያቱ ደግሞ በስምጥ ሸለቆው የሚገኘው እሳተ ጎመራ አቀዝቅዘው የያዙት በአካባቢው የሚገኙ ሐይቆችና የውሃ አማራጮች ናቸው” ብለዋል ።

በተለይ የዝዋይ ሐይቅ የአትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች ፣ ትላልቅ የአበባ ልማት ድርጅቶች ፣ህገወጥ ዓሳ አስጋሪዎችና የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ከአቅሙ በላይ ጫና እያሳደሩበት መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል ።

“የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ቀኑን ሙሉ አቧራ ለመከላከል በቦቴዎች ከሐይቁ ውሃ እየቀዳ በመንገዱ ላይ በማፍሰስ ተጨማሪ ጫና እያሳደረ ነው” ተብሏል ።

ከአርሲ ከታርና ከጉራጌ መቂ ወንዞች ወደ ዝዋይ ሃይቅ ይገባ የነበረው ንፁህ ውሃ በየአካባቢው በሚካሄዱ የመስኖ ልማቶች ተቆርጠው እየቀሩ መሆናቸው ደግሞ ለሃይቁ ብክለትም ሆነ ለውሃ መጠኑ መቀነስ አሉታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ዶክተሩ አያይዘው ገልፀዋል ። 

የ67 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ አቶ አቶ ጋዲሳ እሬሳ    ከወጣትነታቸው ጀምሮ በዓሳ ማጥመድ ስራ ማሳለፋቸውን ገልፀው “የዝዋይ ሐይቅ እንደ አሁኑ ተጎድቶና ተጎሳቅሎ አይቼው አላውቅም” ብለዋል ።

“ያለማንም ተቆጣጣሪና ጠባቂ ማንም እየመጣ እንደፈለገው የሚጠበቀምበት ሐይቅ በመሆኑ የውሃ መጠኑ እየቀነሰ ፣ የዓሳ ምርቱ ደግሞ እየጠፋ በመምጣቱ ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል” ሲሉ አዛውነቱ ተናግረዋል ።

የዝዋይ ባቱ ዓሳ አጥማጅ ማህበር ፀሀፊ አቶ ደራሮ ሆራ በበኩላቸው “የዝዋይ ሀይቅ ከአቅም በላይ ጫና የበዛበትና ለመጥፋት አደጋ የተጋለጠ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ የሚያስፈልገው ነው” ይላሉ ።

ኑሯቸው በዝዋይ ሀይቅ የዓሳ ምርት ላይ የተመሰረተ በ14 ማህበራት የተደራጁ በርካታ ሰዎች ሐይቁ ባጋጠመው ችግር ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ እያጡ መምጣታቸውን አስረድተዋል ።

ሐይቁ መልሶ እንዲያገግም በሚደረገው ጥረት ዓሳ አጥማጅ ማህበራት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ከመስኖ ጋር ተያይዞ የሚታየው ልክ ያጣ የውሃ አጠቃቀም ሊታሰብብት እንደሚገባ አሳስበዋል ።

የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ለማ አበራ እንዳሉት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የሃይቁን ጫና ለመቀነስ መልሶ እንዲያገግም የሚያደርጉ ጥናቶችና ምክረ-ሃሰቦች እየቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም