ከ81 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደቄያቸው ተመልሰዋል

60

አሶሳ ግንቦት 10 / 2011በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰባት ወረዳዎች በተከሰተ ግጭት የተፈናቀሉ  ከ81 ሺህ በላይ ሰዎች ወደቄያቸው ተመለሱ።

በክልሉ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከካማሽ ዞን አምስት ወረዳዎች፣ ከአሶሳ ዞን ኦዳቡልድግሉ ወረዳና ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል፡፡

ተፈናቃዮቹ  ወደ መኖሪያቸው የተመለሱት ከ116 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መካከልመሆኑን የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ተሲሳ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ  ወደ መኖሪያቸው ባለፉት ተከታታይ ወራት በተደረጉ የህዝብ ለህዝብ ውይይት ተከትሎ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት እስካሁን ለተፈናቃዮቹ 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም  አስታውቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን  በማስተባበር በአደጋ የወደሙ ቤቶችን በሳር ክዳን ለመተካት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 35 ሺህ 527 ተፈናቃዮችን በቀጣይ ወራት ወደቄያቸው ለመመለስ ከክልሉ መንግሥትና ከብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር እየተሰራ መሆኑንን አስረድተዋል፡፡

 ወደ ቄያቸው የተመለሱ አርሶ አደሮች በመኸር እርሻ ሥራ  እንዲሰማሩ ቅስቀሳ እየተደረገ  መሆኑን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በግጭቱ ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 36 ሺህ 656 በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፣ 75 ሺህ የሚሆኑት ወደ ኦሮሚያ ክልል የተሰደዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም