የጤና አገልግሎቱን የበለጠ ለማሻሻል ለዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይገባል ተባለ

209

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2011 ባለፉት ዓመታት በተወሰዱ እርምጃዎች እየተሻሻለ የመጣውን የጤና አገልግሎት የበለጠ በማሳደግ የህዝቡን ፍላጎት ማርካት እንዲቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች  በተቻለ መጠን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለፁ።

የኦሮሚያ ክልል የጤና ባለሙያዎች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ያተኮረውና ትናንት የተጀመረው ውይይት ዛሬም ቀጥሏል።

ከትናንት በቀጠለው መድረክ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ደረጀ ዳጉማ መንግስት በአጠቃላይ የአገሪቱ ጤና ዘርፍ ሪፎርም ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ህብረተሰቡም ሰፊ አገልግሎት እያገኘ ቢሆንም ከህዝቡ ቁጥርና ፍላጎት አኳያ የዘርፉን አገልግሎት  የበለጠ ማሻሻል እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ ደግሞ ባለሙያው ለሚያነሳው ጥያቄ  በተቻለ መጠን ምላሽ መስጠት አንዱ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ በትናንትናው ውይይታችው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ከወጭ መጋራት፣ ከስራ ፈቃድ፣ ከጤና ተቋማት አገልግሎት ጥራትና አቅርቦት፣ ከመኖሪያ ቤትና የሙያ መድህን ጋር የተያያዙ ይገኙባቸዋል።

በኦሮሚያ ክልል 1 ሺህ 400 ጤና ጣቢያዎች፣ 81 ሆስፒታሎች፣ 2 ሺህ የጤና ኬላዎች እንደሚገኙና በጤና ተቋማቱም 72 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።